በበጎ ተግባር ላይ ተሰማርተው አርአያነት ያለው ተግባር የከወኑ የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች ተግባራቸው ለሌሎች አስተማሪ በመሆኑ እውቅና እና ሽልማት እንደተበረከተላቸው የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ጉልህ የሰብአዊነት ተግባር ለፈጸሙ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች እውቅና እና ሽልማት አበርክቷል፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ በበጎ ተግባር ላይ ተሰማርተው አርአያነት ያሳዩ የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች ተግባራቸው ለሌሎች አስተማሪ በመሆኑ ሽልማት እንደተበረከተላቸው ገልጸዋል፡፡
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ደንብ አስከባሪዎች የተሰማሩበትን አላማ የሚያሳኩ፣ ዜጎችን በእኩል ዓይን በማየት እና ሰብአዊነትን በማስቀደም የሚሰሩ ናቸው ብለዋል።
በአቃቂ ቃልቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 የሚገኙ፤ ጉድጓድ ውስጥ የወደቀን መንገደኛ በማንሳት መልካም ተግባር የፈፀሙ ሁለት ደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች ያከናወኑት የሰብአዊነት ተግባር ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መሰራጨቱን ተከትሎ የእውቅና እና ሽልማት የመስጠት ስነ-ስርዓት ተከናውኗል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ደንብን ከማስከበር ተግቧሯ ጎን ለጎን የደንብ ማስከበር ዩኒፎርም በመልበስ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የደንብ ማስከበር ተግባራትን የማስተዋወቅ ስራዎችን የምትሰራ የደንብ ማስከበር ኦፊሰርም ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡
ከተሸላሚ የደንብ ማስከበር ኦፊሰሮች መካከል ሌንሳ ከቤ፣ ተስፋሁን ሳሙኤል እና ይርጋለም አበባው የፈጸሙት የሰብዓዊነት ተግባር ስላሸለማቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ ሌሎችንም ለበለጠ ሰብዓዊነት እንደሚያነሳሳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ደንብ አስከባሪዎች ከተሰማሩበት ዋና ተግባራቸው ባሻገር ሰብዓዊነትን አስቀድመው አርአያነት ያለው ተግባር መስራታቸው ሊበረታታ እንደሚገባው በመርሐ-ግብሩ ተመላክቷል፡፡
ባለስልጣኑ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በተሰማሩት የደንብ አስከባሪ ኦፊሰሮች አማካኝነት ደንብ መተላለፍን መከላከልና ሰላምና ፀጥታን የማስከበር ተግባራትን እየተወጣ ይገኛል፡፡
በፈቃዱ ምስጋናው