የግብጽ የአባይን ውሃ ለብቻ የመጠቀም የቅኝ ግዛት እሳቤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስኬት ያበቃለትና የተቋጨ ጉዳይ መሆኑን የሐረማያና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ገለጹ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በብዙ ጫና እና ውጣ ውረድም ውስጥ ሆኖ በመንግስት ጽኑ አቋምና በዜጎች ብርቱ ጥረት ግንባታው መጠናቀቁ ይታወቃል።
የግንባታው ሂደት መሰናክል እንዲገጥመው በተለይም የግብጽ እጆች ያልደረሱበት ቦታ ባይኖርም ኢትዮጵያ በፅናት ሃብቷን አልምታ መጠቀም ጀምራለች።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ስራ ከጀመረም በኋላም ግን የግብጽ ጠቅልሎ የመጠቀም ፍላጎትና በርካታ ማደናገሪያዎችን የማንሳት ጉዳይ አሁንም አልቆመም።
የግብጽ ዘመን የተሻገረ ጠላትነትና የማደናገር ጉዞ የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ እንኳን ለምን አልቆመም በማለት የኢዜአ ሪፖርተር በሐረማያ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ተገኝቶ ምሁራንን አነጋግሯል።
ምሁራኑ በአስተያየታቸው የግብጽ የአባይን ውሃ ለብቻ የመጠቀም የቅኝ ግዛት እሳቤ ያበቃለትና በዚህ ዘመን የማይታሰብ ቢሆንም የተፋሰሱ ሀገራት የበይ ተመልካች ሆነው እንዲቀጥሉ አሁንም ፍላጎት አላት ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ይሁን እንጂ የግብጽ የአባይን ውሃ ለብቻ የመጠቀም የቅኝ ግዛት እሳቤ በህዳሴ ግድብ ስኬት ያበቃለትና የተቋጨ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ መሀመድ ሀሰን (ዶ/ር)፤ የአባይን ወንዝ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለው የግብጽ የቅኝ ዘመን አካሄድ አሁን ላይ ያከተመ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ የበላይነትና የልማት ስኬቱ ወደ ኋላ ሊመለስ የማይችል የማንሰራራት ሂደት ላይ በመሆኑ የግብጽ መሰረተ ቢስ ውንጀላ እና የማደናገሪያ ሃሳብ ትርጉም የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ ከራሷ የሚመነጨውን የአባይ ወንዝ ሳትጠቀምበት ዘመናት መንጎዳቸው የሚያስቆጭ ቢሆንም አሁን ላይ ታሪክ የቀየረ እና የይቻላል መንፈስን ያበሰረ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ ናኒ ደበሌ፤ ለዘመናት እየተመለከትነው ሲፈስስ የኖረው የአባይ ወንዝ አሁን ላይ መብራት አብርቶልንና ዓሳ አብልቶን እያለፈ መሆኑ ትልቅ የታሪክ እጥፋት መሆኑን ገልጸዋል።
የአባይ ወንዝ ኢትዮጵያን አልምቶ የመጓዝ ዓላማ ቢኖረውም ኢትዮጵያ ለምን ተጠቀመች በማለት ግብጽ የያዘችው ጠቅልሎ የመጠቀም አባዜ በግድቡ ግንባታ መቋጫ ያገኘ መሆኑን አንስተዋል።
የአባይ ተፋሰሱ ሀገራት በጋራ ለመጠቀም የደረሱት የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ አብሮ የመልማትና በጋራ የመጠቀም እንጂ አግላይነትን የሚቀበል ባለመሆኑ በዚሁ መንገድ መጓዝ ተገቢ መሆኑን ምሁራኑ አስረድተዋል።