የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉ ተገለፀ

You are currently viewing የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉ ተገለፀ

AMN – ጥቅምት 08/2018 ዓ.ም

የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባዔው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የፌዴራልና ክልሎች የጤናው ዘርፍ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በ2017 በጀት ዓመት የመድኃኒት አቅርቦት ሰንሰለቱን ለማጠናከር የሚያስችል የአዋጅ፣ አሰራር ስርዓት ማሻሻያ ተደርጓል።

የመድኃኒት አቅርቦት ተደራሽነት ላይ የተደረገው ማሻሻያ የተራዘመ የግዢ ሂደት ላይ ለውጥ ማምጣት ማስቻሉንም አስረድተዋል።

ከመንግስትና አጋር አካላት ጋር የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

ከተቋማት ጋር ውል የተገባለት አቅርቦት ስርዓት በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 68 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ መድኃኒትና ሕክምና ግብዓት መሰራጨቱን ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ከ22 ሺህ በላይ የመንግስት ተቋማት ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የአቅርቦት ሰንሰለቱን ለማዘመንና የሀገር ወስጥ አምራቾችን ለማበረታታት የሚያስችል ስራ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ድርሻ 41 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ፈጣንና ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review