ከመብራት ክፍያ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ደንበኞች መከተል የሚገባቸው አማራጭ መፍትሔዎች መኖራቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ይሄይስ ስዩም አመላክተዋል፡፡
በመብራት ክፍያ ጉዳይ ላይ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የአገልግሎቱ የሽያጭ እና ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ይሄይስ ስዩም፤ ደንበኞች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች የተሰናዱ መፍትሔዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ቆጣሪ ሳይነበብ ያለ አግባብ ከፍተኛ ፍጆታ የተጠየቁ ደንበኞች በፍጥነት ቢያመለክቱ ክፍያ ለመክፈል የጊዜ ገደብ የሚሰጥበት አግባብ መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ደንበኛ በራሱ ሳይሆን በተቋሙ የአሰራር ችግር የተፈጠረበትን ጫና በተመለከተ የጊዜ ገደብ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን ያመላከቱት ዳይሬክተሩ፣ ሪጅኖች እንደ ገንዘቡ መጠን የ3 ወር የጊዜ ገደብ መስጠት እንደሚችሉና ወደ ሥራ አስፈፃሚ ሲመጣም እስከ 6 ወር የጊዜ ገደብ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል፡፡
ደንበኛው ከዚህም ባለፈ እስከ አንድ ዓመት እፈልጋለሁ የሚልም ከሆነ ሥራ አስፈፃሚው በተሰጠው ስልጣን የሚስተናገድበት ሥርዓት ተበጅቶለት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን ከከፈላችሁ በኋላ ነው የሚታየው የሚባል አሰራር አለመኖሩን ጠቁመዋል፡፡

ደንበኞችም እንደነዚህ አይነት ነገሮች ሲገጥማቸው እዛው ማመልከት እንደሚችሉ የገለጹት አቶ ይሄይስ፤ ለዚህም ደግሞ ፊት ለፊት መቅረብ ሳይጠበቅባቸው ድርጅቱ ባሉት የቴሌግራም እና የፌስቡክ ገፆች ማድረስ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡
የተቋሙ ዲጂታል ሚዲያ ክፍልም የቀረቡ ሃሳቦችን ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች በማጋራት መፍትሄ እንዲሰጥባቸው የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም ነው ያመላከቱት፡፡
ቆጣሪ ላይ የሰፈረው የኃይል ፍጆታ በትክክል ተነቦ ለደንበኞች ቢል መቅረብ እንደሚገባው የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን ቆጣሪያቸው የማይነበብ ከሆነ ይህንን ለሚመለከተው አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሪፖርት ማቅረብ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ ብቻ መፍትሄ አይሆንም በማለት ለድህረ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚዎች፣ ደንበኛው እራሱ በቴሌግራም ቦት ንባቡን ቢል እንዲሆንለት ወደ ተቋሙ ሲስተም የሚልክበት ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በሌላም በኩል የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎችን እና ስማርት ሜትር የሚባሉትን ቆጣሪዎች በማስፋፋት አንባቢ ሳይሄድ ቆጣሪዎች ንባባቸውን ቀጥታ በሲስተም ወደ ሰርቨር የሚልኩ ዓይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሥራ ላይ የማዋል ሥራዎችም እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ ለአዲስ አበባ ቅድሚያ በመስጠት የቆጣሪ ቅየራ ተግባራት እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት፡፡
በታምራት ቢሻው