የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ አመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡት ዶክተር ሲዲ ኦልድ ታህ ጋር በስትራቴጂያዊ አጋርነትና የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸዉ ጉዳዮች ዙሪያ ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት አካባቢን ምቹ ለማድረግ ፣ ቁልፍ በሆኑ ዘርፎች ምርታማነትን ለማሳደግ እና የመንግስትን የአገልግሎት አሰጣጥ አቅም ለማጠናከር እየተሰሩ ባሉ የሪፎርም ስራዎች ላይ ለፕሬዝዳንቱ ገለፃ አድርገዋል።
በአዲሱና በግዙፉ የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ አዳዲስ መረጃዎችን ያካተተ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን የተያዘዉን ፕሮጀክት እዉን ለማድረግ የአፍሪካ ልማት ባንክ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
ሲዲ ኦልድ ታህ የአፍሪካ ልማት ባንክ ግሩፕ ፕሬዝዳንት ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት በማስተላለፍ በአመራር ሰጭነታቸው ሙሉ እምነት እንዳላቸው ገልፀው፣ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ዶክተር ሲዲ ኦልድ ታህ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ትላልቅ የሪፎርም አጀንዳዎችን አፈፃፀም አድንቀው፣ ባንኩ የሀገሪቱን ትልቅ የለውጥ አጀንዳ በበጀት ድጋፍ፣ በግብርና እና በመሰረተ ልማት ላይ ኢንቨስት በማድረግ በተለይም የአየር ትራንስፖርት ትስስርን በማጠናከር የቀጠናዊ ትስስርና ውህደት እንቅስቃሴዎች ላይ ድጋፍ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።