ኢትዮጵያ ከኔትዎርክ ኪራይ ወጥታ የራሷ የሆነ ኔትወርክ እንዲኖራት የሚያግዝ የፈጠራ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተማሪ ራጂ ኢብሳ ተናግሯል።
“የእኔ የፈጠራ ሥራ ሀገሬ የራሷ የሆነ ኔትወርክ እንዲኖራት እና እንደ ህዳሴ ግድቡ ኔትዎርኳን ለጎረቤቶቿ እንድትሸጥ ያግዛል” ሲል ተማሪ ራጂ ኢብሳ ከኤ. ኤም. ኤን. ዲጂታል ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል።
ዓለማችን ዛሬ እዚህ የደረሰችው በፈጠራ ስራዎች ነው ያለው ተማሪ ራጂ፣ ከዚህ ቀደም የፈጠረውን ኔትወርክ “ዳምቢዶሎ ኔትወርክ” በማለት እንደሰየመና የፈጠራ ስራውም ውጤታማ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ “ኦሮሚያ ኔትዎርክ” የሚል ስያሜ እንደሰጠውም አስታውቋል።
በወለጋ ዞን ዳምቢዶሎ ወረዳ በሚገኘው የቤዚ ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ራጂ፣ ቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ የፈጠራ ስራውን የሰራበት ቦታ እንደነበረ ተናግሯል።
የዚህ የፈጠራ ስራ አላማ የኔትወርክ ምሰሶዎችን ወጪ በማስቀረት በአነስተኛ በጀት ኔትወርክን በተለያዩ ቦታዎች በማስፋፋት እና ኔትዎርክ ባልተዳረሰባቸው የገጠሪቱ የሀገራችን ክፍሎች እንዲዳረሱ እንደሆነ ያስረዳል።

የመጀመሪያ የፈጠራ ስራውን በ 2013 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያለ ሰርቶ በስኬት ለማጠናቀቅ አራት ዓመታትን እንደፈጀበት በመናገር፣ ለዚህም ስራ ያነሳሳው በሚኖርበት አከባቢ የነበረው የኔትዎርክ ችግር እንደነበር ተማሪራጂ ጠቁሟል።
ለፈጠራ ስራውም በአከባቢው ከወዳደቁ እቆዎች መሆኑንም ያብራራል።
ከዚህ በፊት በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተካሂዶ በነበረው የ”ብሩህ ኢትዮጵያ” ውድድር ላይ በመሳተፍ በዓሸናፊነት ማጠናቀቁንም አንስቷል።
ወደፊትም በኔትዎርክ ጉዳይ ላይ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ሳይንቲስት በመሆን ዓለምን ማገዝ እንደሚፈልግ ገልጿል።
የፈጠራ ስራ የባለቤትነት መብትን የሚጠይቅ በመሆኑ ለፈጠራ ስራው የባለቤትነት መብት ካገኘ፣ ሌላም የፈጠራ ስራ ሊሰራ እንደሚችል አስታውቋል።
ተማሪ ራጂ፣ ቤተሰቦቹ ለፈጠራ ስራዎቹ መሰረት መሆናቸውን ጠቅሶ፣ በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የሰው አልባ (ድሮኖች) የፈለሰፈው መምህር አማኑኤል ባልቻ እና የተለያዩ ሰዎች ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉለትም ጠቅሷል።
በወርቅነህ አቢዮ