የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ዉሃን በመጠቀም የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥና ገበያ ተኮር የግብርና ምርቶችን በስፋት ለማምረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በባሌ ዞን ደሎ መና ወረዳ የሚገኘውን የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት መርቀዋል።
በምርቃ መርሀ-ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ የለዉጡ መንግስት ባለፉት አመታት የአርሶና አርብቶ አደሮችን ምርትና ምርታማነት ለማዳደግና የማህበረሰቡን ኑሮ ከመሰረቱ ለመቀየር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ገልፀዋል፡፡
ከገጠር ልማት ጋር በተያያዘ መንገድና ንጹህ የመጠጥ ዉሃ አገልግሎትን ጨምሮ በኤሌክትሪክና ቴሌኮም አገልግሎት እንዲሁም በሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፎች ከፍተኛ ለዉጥ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
በተለይም በግብርናው ዘርፍ በተሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች የህዝቡን አጠቃላይ ኑሮ መቀየር እንደሚቻል የሚያረጋግጡ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በባሌ ዞን የሚገኘዉ የወልመል ወንዝ መስኖ ልማት ፕሮጀክት እና በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኘዉ የጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ከአራት አመት በፊት መጀመሩን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ክትትልና ድጋፍ ለምረቃ መብቃቱን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ተጠናቆ በመመረቁም ለአካባቢዉን ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የከርሰ ምድርና የገጸ ምድርን ዉሃ በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትላልቅ ፤ መካከለኛና አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ በርካታ ተግባራት መከናወናቸዉን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት አመታት ከ100 ሺህ በላይ የዉሃ ፓምፖች በግልና በመስኖ ልማት ኢንሼቲቭ መቅረባቸዉን የተናሩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህም ስንዴን በመስኖ ማልማት በስፋት ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ባለፈዉ አመት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ መልማቱን እና በዘንድሮዉ አመትም 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለረጅም አመታት ያለምንም ጥቅም ሲፈስ የነበረዉ የወልመል ወንዝ በመንግስት በተሰራው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ተገድቦ ዛ እጅ ሰጥቶ ወደ ልማት መግባቱን ያበሰሩት አቶ ሽመልሽ አብዲሳ ዘንድሮ በክልሉ በሚከናወነዉ የስንዴ ልማት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ካላው ሰፊ የዉሃ ሃብት በመስኖ ሊለሙ የሚችሉ መሬቶችን በስፋት ማልማት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ዉስጥ የህዝቡን ኑሮ መቀየር፤ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እና የግብርና ምርቶችን ለአለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡
የአካባቢዉ ነዋሪዎች ያነሱት የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር በመንግስት በኩል ምላሽ እያገኘ በመሆኑ የአካባቢ ማህበረሰብ ከተረጂነት ተላቆ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የተለያዩ ምርቶችን ለገበያ ለማቅረብ በትጋት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቱ ግንባታ እውን መሆን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትንም አመስግነዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ