ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት የጋራ ሥራችን ኃብቶቻችንን መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በኃብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው ሲሉ ገልጸዋል።
በኃብት ስጦታ አንፃር ስንመለከት ኢትዮጵያ ለሁሉም የሚበቃ ኃብት እንዳላት እናውቃለን።
በባሌ ዞን ከተለያዩ አመራሮች ጋር ያደረግነው ጉብኝት የመጨረሻ መዳረሻ አስደማሚው የፊንጫ ሀበራ ፏፏቴ ሆኗል።
በግርማ የሚወርደው ፏፏቴ ወደ ሶፍኡመር የዋሻ ሥርዓት የሚደመረውን የወይብ ወንዝ የሚቀላቀል ነው።
የኢትዮጵያ ቀይ ቀበሮ የሚገኝበት ይኽ አስደናቂ ከባቢ ድንቅ የአዕዋፍ መገኛና በቅርቡ የዋሻ መስህብ የተገኘበት እንዲሁም የራፉ ውብ የዐለት ደን አቅራብያ የሚገኝ ነው ብለዋል።
በቅርቡ በአካባቢው የሚገነባው ማረፊያ ሲጠናቀቅም ለጎብኝዎች የበለጠ ሳቢ እና ምቹ ይሆናል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በጉብኝቱ የተሳተፉ የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ ኃላፊዎች በጉብኝቱ የተመለከቱት የተፈጥሮ፣ የባሕል እና የሰው ኃብት ከፍ ያለ መነሳሳትን ፈጥሮላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
የጋራ ሥራችን እነዚህን ኃብቶቻችንን መግለጥ፣ ማሳደግ፣ በኃብቶቹ ላይ በመጨመር ቀጣዩ ትውልድ ችቦውን ተረክቦ እንዲቀጥል መሠረት መጣል ነው። ኢትዮጵያ በርግጥም የተትረፈረፈ ኃብት ምድር ናት። እንሰባሰብ። ለማለም እንድፈር። የጋራ ነጋችንን በጋራ እንገንባ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል።