በኢትዮጵያ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ የተያዙ ሀገራዊ ግቦች እንዲሳኩ ህዝቡን በንቅናቄ የማሳተፍ ስራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
ብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት በህዝብ ንቅናቄና የፓርቲ ስራዎች አፈጻጸም ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ በዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዛሬው ውይይት ማጠቃለያ ላይ እንዳሉት፤ ዘርፎች በሩብ ዓመቱ ያከናወኑት ስራ የሚበረታታ ነው።
የተሻለ አፈጻጸምን ማስቀጠል፤ ክፍተት ያለበትን ለመሙላት ርብርብ ማድረግ ይገባል ያሉት አቶ አደም ፋራህ ወጥ የሆነ አፈጻጸም እንዲኖር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የተገኙ ውጤቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ አቅሙ የተገነባ አመራርና አባል ወሳኝ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ የአመራርና አባላት አቅም ግንባታ ስራዎች በትኩረት ሊከናወን ይገባል ብለዋል።
ተተኪ አመራር የማፍራት ጉዳይም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቃል ያሉት አቶ አደም፤ ህዝቡን በንቅናቄ በስፋት በማሳተፍ ለግቡ ስኬት ልንረባረብ ይገባል ብለዋል።
ሀገራዊ ልማትና ዲሞክራሲን እውን ለማድረግ የሰላም ግንባታ ስራው ውጤታማ እንዲሆን መስራት እንደሚገባም ነው በአጽንኦት የተናገሩት።
ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያም የህዝብን እርካታ የሚጨምሩ አገልግሎቶች ተደራሽ ማድረግ ላይ ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አመልክተው የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በአጽንኦት መስራት ይገባል ብለዋል።