በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ይህን የተናገሩት የዓለም መሪዎች በተሳተፉበት እና በሰው ሀብት ልማት ላይ በሚያተኩረው የሚኒስትሮች መድረክ ላይ በተሳተፉበት ወቅት ነው።
ስብሰባው የተካሄደው በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ካለው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን ነው።
አቶ አህመድ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግርም በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
በዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ ኢኮኖሚው በሚፈልገው መሰረት የወጣቶችን አቅም ለማጎልበት ትምህርትና ክህሎትን በማጣመር በትኩረት እየሰራች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የዓለም ባንክ ለምስራቅ አፍሪካ ክህሎት ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም እና ለቀጣናዊ ትስስር ፕሮጀክት ስኬት ድጋፉ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ድጋፉ ለትምህርትና ክህሎት ልማት፣ ስራ አጥነትን ለመቅረፍና ለከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት እንዲሁም ለስራ ፈጠራ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም አብራርተዋል።
እነዚህን ተነሳሽነቶች እውን በማድረግ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ስራ ዕድል ለመፍጠር የባንኩ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና አጋርነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ነው በአጽንኦት የገለጹት።
በስብሰባው የሲንጋፖር ፕሬዚዳንት ታርማን ሻንሙጋራትናም እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ከ30 በላይ የሀገራት መሪዎች መሳተፋቸው ተጠቅሷል።