የአልዛይመር በሽታ ምንድነዉ? የበሽታዉ ምልክቶች፤ ህክምናና መከላከያዉስ?

You are currently viewing የአልዛይመር በሽታ ምንድነዉ? የበሽታዉ ምልክቶች፤ ህክምናና መከላከያዉስ?
  • Post category:ጤና

AMN ጥቅምት 10/2018

እድሜቸው ከ65 አመት በላይ የሆናቸው ሰዎች በአመዛኙ የአእምሮ አቅም መቀነስ እንደሚታይባቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህም ሂደት ምናልባትም የመዘንጋት ህመም ወይም በህክምና አጠራሩ አልዛይመር ቅድመ ምልክት እንደሆነ ይገመታል፡፡

በዕለት ተዕለት መስተጋብራቸው ላይ ተደጋጋሚ የመዘንጋት ችግር የሚያጋጥማቸው ሰዎች፣ ራሳቸውን ችለው መሥራትና መንቀሳቀስ ባለመቻል አጋዥ ካስፈለጋቸው የአልዛይመር ህመም ምልክት በመሆኑ ህክምና ሊደረግበት እንደሚያስፈልገው ባለሙያዎች ይገልፃሉ ፡፡

በዕቅድ አለመስራት፣ በማስተዋል ችግር ሀሳብን በሚገባ ለመግለጽ መቸገር እና የቃላት ግድፈት የህመሙ መገላጫዎች መሆናቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ህመሙ ከወንዶች ይልቅ በአብዛኛው ሴቶች ላይ በስፋት እንደሚከሰት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የነርቭ ሀኪምና ተመራማሪ ዶ/ር ያሬድ ዘነበ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከልጅነት ጀምሮ እስከ አዋቂነት እድሜ ድረስ ባለው ጊዜ 40 በመቶ በሽታውን መከላከል ይቻላል፡፡ ፡ በአሁኑ ወቅት እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለይ ልጆች ላይ በቂና ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ በማድረግ አእምሮአቸውን በማሳደግ የበሽታውን ክስተት መከላከል የሚቻል ሲሆን፤ በአንፃሩ ትምህርት የማያገኙ ልጆች ለበሽታው ተጋላጭነታቸው ሰፊ እንደሆነ ነው የሚያመላክተው፡፡

የጐልማሳነት እድሜ ብዙ ጊዜ አዳዲስ ነገሮች የሚጀመሩበት ለምሣሌ አልኮል መጠጥ መጠጣት፣ ሲጋራ ማጨስ፣ በመደባደብ ምክንያት የሚደርስ የጭንቅላት መጐዳት ለዚህ ህመም አጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

እድሜ ከጐልማሳ አልፎ ወደ አረጋዊነት ሲጠጋ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በተለይ ከውፍረት ጋር ተያያዘው የሚመጡ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ የኮሊስትሮል መጨመር እና የልብ ህመም በተለያየ መንገድ አእምሮ ላይ ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል፡፡ ይህም ተጋላጭነትን በእጅጉ ይጨምራል ነው ያሉት ተመራማሪው፡፡

ህመሙ ከተከሰተ በኃላ ከታካሚ ቤተሰቦች መረጃን በመሰብሰብ እና ምርመራ በማድረግ ህመሙ እንዳይባባስ የሚረዳ ህክምና እንደሚሰጥ ዶ/ር ያሬድ ዘነበ ገልፀዋል፡፡ በህክምናው በሚደረግ ምርመራ የበሽታውን አይነትና ደረጃ የመለየት ሥራ ይሠራልያሉት ተመራማሪው፤ ይህም በሽታው ገና እየጀመረ ከሆነ መዳን የሚችል በመሆኑ በማከም ማዳን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

በሁሉም የዕድሜ ክልል ላይ ለሚገኙ ሰዎች ግንዛቤን በመፍጠርና የአኗኗር ዘይቤን በማስተካከል ህመሙ እንዳይከሰት ከወዲሁ መከላከል እንደሚቻልም ተመራማሪው አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ የእንቅልፍ ሰዓትን አለማዛነፍ እና ተከታታይነት ያለው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሽታውን ለመከላከል መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ በመመገብ፣ ጨው እና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን በመቀነስ ጤናማ የሆነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል የበሽታው ክስተት ለመቀነስ ይረዳል፡፡

ጭንቅላት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን መቀነስ ከዛ ባለፈ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በማከም እና በመከላከል የበሽታውን ክስተት መቀነስ ይቻላል፡፡ ሌላው በመንግስት በኩል የታገዘ የአካባቢ ብክለትን መከላከል እና ማህበራዊ መስተጋብርን ጤናማ ማድረግ ለበሽታው ተጋላጭነትን እንደሚቀንስ ዶ/ር ያሬድ ከኤ. ኤም.ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review