የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ታላቅ ሰው አጣች ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ አክሬን ሽኝት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዛሬ መሪር የሃዘን ቀን ነው ሲሉ የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀው፤ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ በህይወት ዘመናቸው ማስተዋልን እና ትእግስትን ካስማቸው እና ድንኳናቸው አድርገው የኖሩ ታላቅ እና ዕንቁ ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት መሪ ነበሩ ሲሉ ገልፀዋቸዋል ።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ እውቀታቸውን ለመላው ኢትዮጵያዊ ሳይሰስቱ ሲያስተምሩ የኖሩ ዕንቁ መሪ መሆናቸውን በመግለጽ፣ በጎ መምህር እና በጎ አባት እንደነበሩም አንስተዋል።
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ በእውቀታቸው ፣ በጥበባቸው እና በእርጋታቸው ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ማስተዋል፣ ማጤንን ፣ አቅል ማድረግን እየኖሩበት አስተምረው ያለፉ መምህር እንደነበሩ አመላክተዋል።
በወርቅነህ አቢዮ