በአዲስ አበባ ከተማ ከጥቃቅን የንግድ ዘርፎች እስከ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ድረስ ያሉ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ከጥቅምት 1 ቀን ጀምሮ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ቆጠራው የሚካሄደው የፕላንና ልማት ቢሮ ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ጋር በመተባበር ነው ።
ለኢኮኖሚ ድርጅቶች በከተማዋ 5506 የቆጠራ ቦታዎች የተዘጋጁ ሲሆን ከ5ሺህ በላይ ሰራተኞች መረጃውን እየሰበሰቡ እንደሚገኙ በመግለጫው ተጠቁሟል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ቆጠራው የከተማዋን እና የሀገሪቱን ጥቅል ኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር በማነፃፀር ደረጃውን ከማወቅ ባሻገር የግል አልሚዎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመጠቆም ያግዛል ብለዋል፡፡
አቶ አደም ቆጠራው የአገልግሎት፣ የኢንዱስትሪና የከተማ ግብርና የኢኮኖሚ ዘርፎች ለአጠቃላይ የሀገር ምጣኔ ሀብት ያላቸዉን አበርክትዎ ለማወቅና የዘርፎች የተናጠል ድርሻን ወቅታዊ ለማድረግ የሚረዳ ስታቲስቲካላዊ መረጃ ለማግኘት፤ ብሎም በቀጣይነት ለሚከናወኑ ዘርፈ ብዙ ጥናቶችና ለፖሊሲዎች ግብዓት የሚሆን የተሟላ መረጃ ለማግኘት ነው” ብለዋል።
በወንድማኝ አበበ