ሰላማችንን ጠብቀን፣ እየተቻቻልን የፖለቲካ ስርዓታችንንም አስተካክለን ከሄድን ብሩህ የሆነ የወደፊት ዕድል እንዳለ ይታየኛል ሲሉ ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ አመራሮች ጋር በሶፍ ኡመር ዋሻ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ፣ ወደ ባሌ ሶፍ ኡመር ለጉብኝት ሲጋበዙ የገመቱት ነገር እንዳልነበር ያነሱ ሲሆን፣ ነገር ግን ባሌ ከደረሱ በኋላ ያልጠበቁትን ነገር ማየታቸውን ተናግረዋል።
ከድሮ የሥራ እና የትግል ጓደኞቻቸው ጋር ለመወያየት እንዲሁም አብረው ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ ዕድል ማግኘታቸውንም ነው የገለጹት።
እንደ ሌሎች ጓደኞቻቸው ብዙም ባይመላለሱም መከላከያ እያሉ ወደ ባሌ ይሄዱ እንደነበር ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ የዚህን ያህል ስፋት፣ የመሬት ልማት፣ የውሀ ብዛት፣ ልዩ ስነ ምህዳር ያለው እና የትኛውንም ዓይነት ሥራ ለመስራት የሚያስችል የተመቸ ሁኔታ ያለው መሆኑን እንደማያውቁ ተናግረዋል።
ስለ ሶፍ ኡመር ዋሻም በወሬ ይሰሙ እንደነበር በማስታወስ፣ ነገር ግን 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው የዋሻ ውስጥ ሰፈር መኖሩ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።
አሁን ደግሞ አደረጃጀቱ እና ሥርዓቱ በሚመች መንገድ የተዘጋጀ ሆኖ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
አሁንም ችግሮች እንዳሉ አውቃለሁ ያሉት ሌተናል ጀነራል ፃድቃን፣ እነዚህን ችግሮች የፖለቲካ ሥርዓታችንን በማስተካከል፣ በመቻቻል እና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን ሳንል ለሀገር የሚጠቅም ነገር በመስራት እንፈታቸዋለን ነው ያሉት።
በታምራት ቢሻው