ለምን ለማኝ ሆንን የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልቻልኩም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ለምን ለማኝ ሆንን የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልቻልኩም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ጥቅምት 10/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በስፋት እየተከናወኑ ካሉ የልማት ሰራዎች መካከል አንዱ የተፈጥሮ ሃብትን በማልማት የቱሪዘሙን ዘርፍ ማነቃቃትና የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ሲሆን፣ ለዚህም ገበታ ለሃገር እና ገበታ ለትውልድ ተጠቃሾች ናቸው ፡፡

መንግስት በሃገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማት እያከናወነ ካላቸው ተግባራት አንዱ መገለጫ በሆነው የሁለቱ ባሌ አካባቢዎች የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ የተሰሩ ስራዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በተለያየ ደረጃ በሚገኙ አመራሮች ተጎብኝተዋል፡፡

ከጉብኝት ባለፈ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ እና በልዩ መልክ ሳቢና ውብ ሆኖ በተሰናዳው የሶፍ ዑመር ዋሻ ከቀድሞ እና ከአዳዲስ አመራሮች ጋር እየተከናወኑ ባሉ እና በአካባቢው ባዩት የልማት ስራዎች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለምን ለማኝ ሆንን የሚለውን ጥያቄ መመለስ አልቻልኩም ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ ባሌ ያየነው ሃብት ተፈጥሮ ስለኛ ስለአሁኑ ትተን ነቅቶ ከመባላት ወጥቶ በመስራት ሃገሩን ከልመና የሚያወጣ ትውልድ የምንፈጥረው መቼ ነው በማለት ሃሳባቸውን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ነቅተን በሃገራችን ሰርተን ሌላን መርዳት ሲገባን እኛ ያለንበት ሁኔታና የተሰጠን ነገር ግን አብሮ አይሄድም ሲሉ ነው የገለፁት ፡፡

ሁሉንም ዓለም የማየት ዕድል አግኝቻለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በሁሉም ዓለም ሻል ያሉ የሚባሉ ነገሮችን ለማየት ዕድል አግኝቻለሁ ነገር ግን በህይወት ዘመኔ እንደ ባሌ ያለ ምድር ሁሉም ነገር በአንድ ሰፍራ ያለው በኢትዮጵያ በአፍሪካም በየትም ዓለም ውስጥ አይቼ አላውቅም ሲሉ አካባቢው ምን ያክል በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህ ተሰጥቶን ግን ልጆቻችን ጫማ የላቸውም ቤቶቻችንም ያሳዝናሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተወያይተን ትውልድ ነቅቶ ተምሮና እኛ ያበላሸነውን እና ያላስተካከልነውን አርቆ እና አርሞ ለነገይቱ ኢትዮጵያ ተስፋ አንዲሆን ለነገ ዘር የሚሆን ዘሩ በቅሎ በኛ ዕድሜ ወይንም ከኛ በኋላ በትውልድ ውስጥ የተሻለ ሃገር ለማየት የሚያስችል ነገር የሚፈጥር ሃሳብ ያስፈልጋል ነው ያሉት ፡፡

ካለንበት ሁኔታ ወጥተን ሃገር ሰርተን ሃገር ጥሎ የሚሰደድ ትውልድ ሳይሆን ወደ ሃገር የሚሰደድ ማወቅ የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ልንሰራ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review