አርሰናል ከ አትሌቲኮ ማድሪድ :- በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙበት ጨዋታ

You are currently viewing አርሰናል ከ አትሌቲኮ ማድሪድ :- በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙበት ጨዋታ

AMN-ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሊግ ፎርማት 3ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ።

ዛሬ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል በሜዳው ኤምሬትስ አትሌቲኮ ማድሪድን የሚያስተናግድበት ይጠበቃል።

መድፈኞቹ በቻምፒየንስ ሊጉ አትሌቲክ ቢልባኦ እና ኦሎምፒያኮስን በተመሳሳይ 2ለ0 በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ አድርገዋል።

አርሰናል ለዛሬው ጨዋታ አዲስ የጉዳት ዜና የለበትም ፤ በአንፃሩ ተከላካዮቹ ቤን ዋይት እና ፒዬሮ ሂንካፒዬ ወደ ልምምድ ተመልሰዋል።

ፕሪምየር ሊጉን በሦስት ነጥብ ልዩነት እየመራ የሚገኘው አርሰናል ከአትሌቲኮ ማድሪድ ጋር በቻምፒየንስ ሊግ ሲገናኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በ2017/18 የውድድር ዓመት በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ተገናኝተው አትሌቲኮ ማድሪድ በደርሶ መልስ 2ለ1 ማሸነፍ ችሎ ነበር።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ ከስፔን ክለቦች ጋር ባደረጋቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች ሁሉንም አሸንፏል።

በሌላ በኩል አትሌቲኮ ማድሪድ ወደ እንግሊዝ አቅንቶ ካደረጋቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ድል የቀናው በአንዱ ብቻ ነው።

የሁለቱ ክለቦች ተጠባቂ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ይጀምራል።

ባየር ሊቨርኩሰን ከ ፓሪሰን ዠርማ ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከ ቤኔፊካ ፣ ፒ ኤስ ቪ አይንዶቨን ከ ናፖሊ ፣ ቪያሪያል ከ ማንችስተር ሲቲ ፣ ኮፐንሀገን ከ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ፣ ኡኑዮን ሴንት ጂልዋስ ከ ኢንተር ሚላን እንዲሁም ባርሰሎና ከ ኦሎምፒያኮስ ዛሬ የሚከናወኑ ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው።

ባርሰሎና ከ ኦሎምፒያኮስ የሚያደርጉት ጨዋታ ምሽት 1:45 ሲጀምር ሌሎቹ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምሩ ይሆናል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review