በመዲናዋ እየተበራከቱ ያሉት የመዝናኛ አማራጮች

You are currently viewing በመዲናዋ እየተበራከቱ ያሉት የመዝናኛ አማራጮች

AMN- ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ እየተበራከቱ የመጡት የመዝናኛ ሥፍራዎች በእረፍት ቀናት ለነዋሪዎች ሰፊ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

አብዛኛው ማህበረሰብ ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ የእረፍት ቀናትን በተለያዩ ሁነቶች ያሳልፏቸዋል፡፡ ሰዎች በእነዚህ ቀናት ከሚያከናውኗቸው ተግባራት መካከል አንዱ ከቤት ወጣ ብሎ መዝናኛ ሥፍራዎች ማሳለፍ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አዲስ አበባ ከተማ ከዚህ በፊት የነበራት ገፅታ ለተዝናኖት ምቹ ያልሆነና አማራጭ የመዝናኛ ሥፍራም በቅጡ ያልነበሯት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመዲናዋ የመዝናናት ባህል እምብዛም እንደነበር ይነገራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኮሪደር ልማት ሥራውን ተከትሎ አማራጭ የህዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች በማስፋት ሰዎች የእረፍት ጊዜያቸውን በመዝናናት ማሳለፍ የሚያስችሉ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከተሰሩ አማራች የህዝብ መዝናኛ ሥፍራዎች መካከልም የክብር ዶክተር አርቲስት አሊቢራ አደባባይ አካባቢ ያለው ፓርክ አንዱ ነው፡፡

በዚህ ፓርክ በቅዳሜ እና እሁድ የእረፍት ቀናት በርካታ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን እየተዝናኑ ያሳልፋሉ፡፡ ፓርኩ በርካታ የመዝናኛ አማራጮች ያሉት ሲሆን፣ ከአማራጮቹም መካከል የህፃናት የኳስ መጫወቻ ሜዳ አንዱ ነው፡፡

በዚህ ሥፍራ ህፃናት በነፃነት የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በአካልም በአዕምሮም ብቁ ሆነው እንዲያድጉ በማስቻል ረገድ ትልቅ ሚና ያለው ነው፡፡ ፓርኩ እንቅስቃሴ እያደረጉ በተለያዩ አማራጮች የሚዝናኑበት ብቻ አይደለም፣ የደከመው የሚያርፍበት እና ከወዳጅ ዘመድ ጋር ቁጭ ብሎ የሚጨዋወትበትን ዕድል ያመቻቸ ነው፡፡

በፓርኩ ውስጥ ከጓደኛቸው ጋር ቁጭ ብለው ሲያወጉ የነበሩት ወ/ሮ ፀዳለ ሁሴን፣ አካባቢው ከዚህ ቀደም አቧራ የሆነና መጥተው ሊያርፉበትና ሊዝናኑበት ቀርቶ በሩጫ አልፈው የሚሄዱት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተለይ ለትልልቅ ሰዎች ታክሲ ለመጠበቅም ይሁን እንዲሁ ለማረፍ አካባቢው ምቹ ሆኖ መገንባቱን የተናገሩት ወ/ሮ ፀዳለ፣ ፓርኩ እየሰጠ ያለው አገልግሎት ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች በፓርኩ ሲገለገሉ የነበሩ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው ሰዎችም ቦታው ከዚህ ቀደም ተዘዋውረው ሊዝናኑበትና ቁጭ ብለው ሊጨዋወቱበት ቀርቶ በአጠገቡ ለማለፍ የሚከብድ፣ ፍጹም ለጤና ጠንቅ እንደነበር በማንሳት አሁን ግን እጅግ ያማረና ምቹ ለጤናም ተስማሚ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡

ዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ እና አቅመ ደካሞችም ያለ ምንም ክፍያ በነፃነት ተዝናንቶ የሚገባበት መሆኑም ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሩቅ ቦታ ልጆቹን ይዞ ሄዶ ለማዝናናት ለማይችልም ሰው ሥፍራው ጥሩ አማራጭ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review