ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ የመንግስት አመራሮች ጋር ባሌ በሚገኘው በሶፍኡመር ዋሻ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የሶፍኡመር ዋሻንና ሌሎችንም በአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በማየቴ በአንድ በኩል ተስፋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቁጭት ተሰምቶኛል ብለዋል፡፡
በሶፍኡመርና በአካባቢው በአጭር ጊዜ የተከናወነው የልማት ስራ፣ መንግስት በከተማና በገጠር በሁሉም አካባቢዎች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እና ኢትዮጵያ ትክክለኛ የልማት አቅጣጫን እየተከተለች መሆኑን ያየንበት ነው ብለዋል፡፡

ፀጋን መሰረት አድርጎ እና አውቆ የመምራት ጥበብ በጣም ትልቅ ችሎታ መሆኑንም ሚኒስትሯ አክለው ተናግረዋል፡፡
ባሌ ላይ ያየነው ነገርም እስከ አሁን እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች ሌላኛው ገጽታ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡
የሶፍኡመር ዋሻን የማየት ባገኙት ዕድልም ያለንን ነገር በውል አለመረዳት እና አለማወቅ በድህነት ውስጥ እንድንኖር እንዳደረገን ትምህርት ወስጃለሁ ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን