የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት አመት በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእዉቅና እና የሽልማት መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፉት 7 አመታት በመዲናዋ ከ42.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት የበጎ ፈቃድ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች፣ እና ሌሎችም ነዋሪዎች ከበጋ እስከ ክረምት አመቱን በሙሉ የሚዘልቅ የበጎ ፈቃድ ተሳትፎ እያከናወኑ እንደሚገኙም ከንቲባዋ አመላክተዋል፡፡
በመዲናዋ የሚካሄደውን የበጎ ፈቃድ ተግባር እድሜ፣ ጾታ፣ የገቢ መጠን ሳይወስነው ሁሉም በአንድነት በመሆን የህይወት ዘይቤ እያደረገው መምጣቱንም ከንቲባዋ አብራርተዋል፡፡
በዚህም ብዙ አቅመ ደካሞች፣ የሀገር ባለውለታዎች፣ ለከፋ የማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍ የሚፈሱ እንባዎችን ማበስና የዘመሙ ጎጀዎችን ማቃናት ተችሏል ብለዋል፡፡

ለዚህ የተቀደሰ ተግባር ከተማ አስተዳደሩ በየ አመቱ እውቅና የሰጠ ሲሆን የዛሬው እውቅናም በ2017 በጀት አመት በበጎ ፈቃድ ተግባር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና እና ሽልማት ለመስጠት መሆኑን ከንቲባዋ ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ይህን ባህል እየሆነ የመጣውን አኩሪ ተግባር ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ እና ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽንና ህግ በማውጣት ማህበራዊ ሀላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ መቻሉንም ነው ከንቲባዋ የጠቆሙት፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የከተማዋ በጎ ፈቃደኞች በአረንጓዴ አሻራ፣ በደም ልገሳ፣በአካባቢ ጽዳት፣ በአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና እድሳት፣ በትራፊክ ህግ ማስከበር፣ በሰላም ሰራዊት፣ በምገባ ማዕከል እና በትልልቅ የመዲናዋ የልማት ስራዎች አመቱን በሙሉ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡
በአስማረ መኮንን