ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሰው ሰራሹን የንጋት ሐይቅን ፈጥሯል

You are currently viewing ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሰው ሰራሹን የንጋት ሐይቅን ፈጥሯል

AMN ጥቅምት 11/2018

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር በመቀየር ጉባን ምቹ የቱሪዝም ስፍራ ማድረጉን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ እና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የጽሕፈት ቤት የሥራ ኃላፊዎች የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጎብኝተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጭበትን አቅም ይዞ ተመርቋል፡፡

ግድቡ 74 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የያዘ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ሰው ሰራሹን የንጋት ሐይቅን ፈጥሯል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ሰብሳቢ መለሰ መና፤ ከ12 ዓመት በፊት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጅምር ላይ እያለ አይተውት እንደነበር አስታውሰዋል።

በወቅቱ ጉባ ከሰውነት ለይ ላብ እንደ ውሃ የሚቀዳባት ሀሩር ምድር ነበረች ብለዋል፡፡

አሁን የሕዳሴ ግድብ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ የአካባቢውን ሥነ ምህዳር ወደ ምድራዊ ገነት ቀይሮታል ብለዋል፡፡

“ዛሬ ያ አስጨናቂ ወላፈን የለም” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፤ የሰው ልጅ የተፈጥሮን ምህዳር ወደሚመች ሁኔታ ማስተካከል እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጉባ ሰማይ ተፈጥሮ ጥቂት ሰጥተዋት በብዙ እጥፍ እንደምትመልስ ያረጋገጠ መሆኑን በማንሳት፤ በወቅቱ የነበረው ሀሩር በነፋሻማ አየር የቀይሯል ብለዋል፡፡

በቀጣይም በንጋት ሐይቅ ዙሪያ ያለው አካባቢ ሲለማ ለሰው ልጆች ኑሮና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሳለጥ የተመቸ ውብ አካባቢ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካሪ ኮሚቴ አባል አብርሃም በርታ(ዶ/ር)፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተባበርን ሀገር መቀየር እንደምንችል አሳይቷል ብለዋል፡፡

ግድቡ አካባቢውን ውብ፣ ለኑሮ ተስማሚ የአየር ጸባይ እንዲኖረው አስችሎታል ብለዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በበኩላቸው፤ የግድቡ ግንባታ ሲጀመር አካባቢው ከ50 ዲግሪ ሴልሼስ በላይ ሙቀት እንደነበር አንስተዋል፡፡

ክረምት ላይ አካባቢው አረንጓዴ ቢሆንም በበጋ ወቅት አስቸጋሪ ሙቀት እንደነበረው ጠቅሰው፤ የንጋት ሐይቅ የአካባቢውን የአየር ሁኔታ ቀይሮታል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን በላባቸውና በደማቸው የገነቡትን ፕሮጀክት ለጉብኝት ምቹ ለቱሪዝም ተስማሚ በመሆኑ እንዲጎበኙትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review