የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል መሆን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር የመፍጠር ስራን የበለጠ እንደሚያጠናክር የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ

You are currently viewing የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል መሆን ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር የመፍጠር ስራን የበለጠ እንደሚያጠናክር የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ

AMN ጥቅምት 11/2018

የኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት አለመግባባቶች የግልግል ዳኝነት ማዕከል አባል መሆን የኢንቨስትመንት ምህዳርን የበለጠ ምቹ ለማድረግና የኢንቨስተሮችን አመኔታ ለመጨመር ጉልህ ፋይዳ እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ማዕከሉ በበኩሉ ለኢትዮጵያ የአባልነት ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ መደረጉ ይታወቃል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን የዓለም ባንክ እህት ድርጅት ከሆነው የዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት አለመግባባቶች የግልግል ዳኝነት ማዕከል(ICSID) ዋና ጸሐፊ ማርቲና ፖላሴክ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ ኢትዮጵያ የግልግል ዳኝነት ማዕከሉ አባል የመሆን ጥያቄና የማፅደቅ ሂደት የሚገኝበት ደረጃ ላይ ያተኮረ ነው።

ኢትዮጵያ ከማዕከሉ ጋር ያላትን ግንኙነት በማጠናከር መንግስት የኢንቨስተሮችን መተማመን ለመገንባት እንዲሁም ተገማች፣ ተጠያቂነት የሰፈነበትና ህግን መሰረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ከባቢ የመፍጠር አጀንዳ ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ተደርጓል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለኢንቨስትመንት የሚመች ምህዳር ለመፍጠር ጠንካራ ቁርጠኝነት እንዳለውም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል መሆን ኢንቨስተሮችን በህግ ማዕቀፎች ላይ ያላቸው መተማመን እንዲያድግና ኢትዮጵያን ከዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት ማህበረሰብ ጋር የበለጠ ለማስተሳሰር ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አመልክተዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባልነት የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳ በተለይም የንግድ ምቹነት ለማሻሻል፣ በግሉ ዘርፍ የሚመራ እድገትን ለማረጋገጥና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የኢንቨስትመንት አለመግባባቶች የግልግል ዳኝነት ማዕከል ዋና ፀሐፊ ማርቲና ፖላሴክ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የማዕከሉ አባል የመሆን ፍላጎት መልካም ጅምር መሆኑን ገልጸው ድርጅቱ የኢትዮጵያ አባል የመሆን ጥያቄዋን በማጽደቅ ሂደት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ አባልነት ሀገሪቱ በኢንቨስትመንት ጥበቃ እና አለመግባባቶችን በህጋዊ መንገድ የመፍታት ሂደት ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን ገቢራዊ ለማድረግ ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች የኢትዮጵያን የአባልነት ሂደት ማፋጠን የሚያስችሉ ተከታታይ ውይይቶችን ለማድረግ እንዲሁም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የኢንቨስትመንት የማሳለጥ ጥረቶች አካል የሆነው የባለሀብቶችን አመኔታ መጨመር ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ እና ማዕከሉ በአዲስ አበባ የቴክኒክ አውደ ጥናት ለማድረግ መስማማታቸው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review