የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ከአቡ ዳቢ ልማት ፈንድ (ኤዲኤፍዲ) ዋና ዳይሬክተር መሃመድ ሰይፍ አል ሱዋይዲ ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሁለቱ ወገኖች በጋራ ልማት እና በኢንቨስትመንት ተሳትፎ ዙሪያ በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ማጠናከር ላይ ያተኮረ ውይይት አካሄደዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የአቡ ዳቢ ልማት ፈንድ ኢትዮጵያ በሀገራዊ ልማት ትኩረት በሰጠቻቸው ዘርፎች እያደረገ ለሚገኘው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸው፤ ፈንዱ ዘላቂ ዕድገትና የሥራ ዕድል መፍጠርን የሚያበረታቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በገንዘብ በመደገፍ ለተጫወተው ሚና ምስጋና አቅርበዋል።
የአቡ ዳቢ ልማት ፈንድ ዋና ዳይሬክተር መሃመድ ሰይፍ አል ሱዋይዲ በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነትን አረጋግጠው፤ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን የሚያሳድጉ እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክሩ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን ለመፍጠር ፈንዱ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለቱም ወገኖች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ልማትን ለማስፈን እና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማስፋፋት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በማረጋገጥ ውይይቱ ተጠናቋል።
በዳዊት በሪሁን