የአሜሪካ ግምጃ ቤት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

AMN- ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስቴር ከአሜሪካ ግምጃ ቤት እና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ጋር የኢኮኖሚ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያይቷል።

በገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ነው ያካሄደው፡፡

በውይይቱ ወቅት በኢትዮጵያ ስላሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች ለአሜሪካ ባለስልጣናት ገለጻ ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትሩ ፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ በመተግበር ያስመዘገበችውን እድገት አጉልተው አሳይተዋል።

አክለውም የአሰራር ግልጽነትን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ አስተዳደርን ለማጠናከር እና የንግድና ኢንቨስትመንት ምህዳርን ለማሻሻል መንግሥት ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ውይይቱ አሜሪካ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጥረቶች ላይ በባለብዙ ወገን የልማት ባንኮች እና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) በኩል የምታደርገውን ቀጣይ ድጋፍ፣ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ማጠናከርን ጨምሮ የጋራ የትብብር ጉዳዮችንም አካቷል።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት እና ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት አድንቀው፤ በቴክኒክ ድጋፍ፣ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ እና ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሽግግር መደገፋቸውን ለመቀጠል ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review