AMN – ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2017 በጀት አመት በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት የእዉቅና እና የሽልማት መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡
በዕውቅናና ሽልማት ስነ-ስርአቱ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ወገኖቻቸዉን ላገለገሉ ግለሰቦችና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮያውያን ዘር ሃይማኖት እና ቀለም ሳይለያቸዉ ብዝሃነታቸዉን ጠብቀዉ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነችውን አዲስ አበባን ለማሳደግ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎም አድንቀዋል፡፡
አፈ ጉባኤዉ በጎ ፍቃደኞች ካደረጉት ተሳትፎ ጎን ለጎን የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ላስተባበሩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በጎ ማድረግ በሰው እና በመንግስት እና በሃገር ያስመሰግናል ፤ ምስጋናና ዕውቅና ብቻ ሳይሆን በጎ ማድረግ ደግሞ ከፈጣሪ ዘንድ በረከት አለው ለዚህ በረከት ስለታደላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
በያለው ጌታነህ