AMN- ጥቅምት 11/2018 ዓ/ም
ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ በተከናወኑ ከ15 በላይ ዋና ዋና አሳታፊ የበጎ ፈቃድ መርሐ-ግብሮች ውጤታማ ሰው ተኮር ሥራዎች በማከናወን በከተማዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልና ተደራሽነቱ እንዲያድግ እየተደረገ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይመር ከበደ ገልፀዋል፡፡
በለውጡ ዓመታት ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ሥራዎችን በመስራት ከተማዋ በማንኛውም የከተሜነት መመዘኛ ስትመዘን እንደ ስሟ አዲስ አበባ ያደረጉ ሥራዎችን ማከናወን በመቻሉ አዲስ አበባ የሀገራችን የብልፅግና ተምሳሌት መሪ መሀን መቻሏንም ነው የተናገሩት፡፡
ባለፉት ሰባት ዓመታት በበጎ ፈቃደኝነት የአቅመ ደካሞችን ቤት ከመጠገንና ቀለም ከመቀባት ተነስቶ፣ የበጎነት መንደሮችን ወደ መገንባት ተሸጋግሮ ከከተማዋ ለውጥ ጋር የሚራመድ ትልቅ ሀሳብና ተግባር መሆኑን ነው ኮምሽነሩ የተናገሩት ፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ባለጸጋዎች፣ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የመንግስት እና የግል ተቋማት በርካታ የበጎ ፍቃድ ሥራዎችን በማከናወን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖችን ከጎናቸው በመሆን አለኝታነታችሁን አረጋግጣችኋል ሲሉም ነው የገለፁት፡፡
ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት በከተማዋ በተከናወኑ ከ15 በላይ ዋና ዋና አሳታፊ የበጎ ፈቃድ መርሐ-ግብሮች ውጤታማ ሰው ተኮር ሥራዎች በማከናወን በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልና ተደራሽነቱ እንዲያድግ መደረጉን ነው ያብራሩት፡፡
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ ሰው ተኮር የበጎ ፍቃድ መርሐ-ግብሮች 40 ሺህ 576 የአቅመ ደካሞች እና የአረጋውያን ቤቶችን በመገንባት 173 ሺህ 530 ቤተሰቦችን የቤት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በድግግሞሽ 5.5 ሚሊዮን በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዕድ በማጋራት ለ133 ሺህ 631 ነዋሪዎች ሦስት ወር እና ከዚያ በላይ ከድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር ትስስር በመፍጠር እንዲሁም 1ሺህ 313 ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት በተለያዩ አማራጮች ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉንም ነው ኮምሸነር አቶ ይመር ከበደ ያመላከቱት ፡፡
ለ297 ሺህ ዜጎች ነፃ የህክምና የተሰጠ ሲሆን፣ በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር 309 ሺህ 102 ዩኒት ደም መሰብሰብ መቻሉንም አንስተዋል፡፡
ለ483 ሺህ 318 ተማሪዎች ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ መደረጉን የገለፁት ኮምሸነሩ በተመረጡ አደባባዮች 40 ሺህ 660 የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ፕሮግራም አገልግሎት መስጠት እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
በታምራት ቢሻው