ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ በጎ ፈቃደኝነት የአዲስ አበባችን ሌላኛዉ መገለጫ ሲሉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ በ 2017 ዓ.ም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከጎናችን የነበሩ ልበ ቀናዎችን ስለ መልካም ተግባራቸዉ አመስግነናል ሲሉ ገልጸዋል።
ዉድ የበጎ ፍቃድ አምባሳደሮቻችን እንኳን ደስ አላችሁ። በዚህ ሰዉ ተኮር በሆነዉ እና በጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አርያነት ተጀምሮ በመላዉ ነዋሪዎቻችን ዘንድ የየእለት ተግባር እና ባህል በሆነዉ የበጎነት ስራ የፈሰሱ እምባዎች ታብሰዋል ፣ ያዘመሙ ቤቶች ተቃንተዋል ፣ የአገር ባለዉለታዎች ፣ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸዉ ፣ ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችንን በመርዳት የኑሮ ጫናቸዉ እንዲቃለል ተደርጓል ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ባለፉት 7 የለዉጥ አመታት ወጣቶቿን ፣ ባለሀብቶቿን ፣ መላዉ ነዋሪዎቿን ፣ የተለያዩ የሙያ ዘርፍ ባለቤቶችን በማስተባበር አመቱን ሙሉ በዘለቀ የበጎ ፈቃድ ተግባር ዉስጥ በማሳተፍ ከ 42 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በበጎ ፈቃድ ተግባር በማሰባሰብ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ተችሏል።
በ2017 ዓ.ም እንዲሁ ከ 16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ ለተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንዲዉል ተደርጓል ።ከዚህ ዉስጥ 2.2 ቢሊዬን አስተዋፅኦ በማድረግ የዘንድሮዉንም ልዩ ሽልማት የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ጉሩፕ ወስዷል።
በዚህ በምድርም በሰማይም ዋጋዉ ከፍ ባለ መልካም ተግባር ዉስጥ በተለያየ መንገድ ያለ ስስት አሻራችሁን ላኖራችሁ ፣ መስጠት ላላጎደለባችሁ ልበ ቀና የከተማችን ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋናዬን አቀርባሁ ብለዋል።
ይህን ትዉልድ ተሻጋሪ አኩሪ የበጎነት ተግባር አጠናክራችሁ እንድትቀጥሉ ጥሪዬን አቀርባለዉ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።