እስራኤል በውሃ ሃብት አስተዳደርና በዘመናዊ ግብርና አሰራር ያላትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ገለፁ።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ መካሄዱ ይታወሳል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ከስብሰባው ጎን ለጎን ከእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትሪች ጋር በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለውን የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ውይይቱ በተለይም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለዉን የኢኮኖሚ እና ኢንቨስትመንት ትብብር የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመምከር እድል የፈጠረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።
አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የእስራኤሉ የገንዘብ ሚኒስትር በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው፣የኢንቨስትመንት ትስስሮችን ለመፍጠር፣በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣በዲጂታል ፋይናንሲንግ፣በውሃ ሃብት አስተዳደር፣በዘመናዊ ግብርና አሰራር ያላትን ዕውቀት እና ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል።
እንዲሁም ሁለቱ አገሮች ለጋራ ዕድገትና ብልጽግና ያላቸውን አጋርነት ለማጠናከር ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።