በኢትዮጵያ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው ቁጭትን የሚፈጥር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች የቀድሞ እና በሥራ ላይ ያሉ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ”የሶፍ ዑመር ወግ” በሚል በሶፍ ዑመር ዋሻ ውይይት አድርገዋል፡፡
ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፣ የባሌ አካባቢ የወንዞቹ ብዛት፣ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ፣ ለግብርና ያለው ተስማሚነት፣ ለታሪክ፣ ለቅርስና ለባህል ጥናት ያለው ምቹነት ጥቅም ላይ አለመዋሉ ቁጭትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ባሌን ያህል ስፍራና በሀገሪቱ የሚገኙ እንደባሌ ያሉ ሰፊ ሀብት፣ ታሪክና ቅርስ ያላት ኢትዮጵያ ተራበች፤ ተቸገረች ሲባል ለምንድነው ብለን አለመነሳታችን የሚያስቆጭ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ድሀው ማን ነው? የእኛ አስተሳሰብ ወይስ ኢትዮጵያ፤ የኛ ድህነት ያለመፈለግ ነው ወይስ የመነፈግ ነው ሲሉም በቁጭት አንስተዋል።
በባሌ ዞን ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ ማየት ብቻውን ኢትዮጵያ ብዙ ሃብት እንዳላት ለመረዳት አዳጋች አይደለም ሲሉም ገልፀዋል፡፡
የእኛ ድህነት የእጦት ነው ወይስ የቅንጦት ያሉት ሚንስትሩ፤ ይህ ትውልድ የሚቀየረው እነዚህን የቁጭት ጥያቄዎች በመመለስ ነው ብለዋል።
በ-በረከት ጌታቸው