የማደግ ዕድላችን በእጃችን ነው ሲሉ የቀድሞ አመራር አቶ ጁነዲን ሳዶ ተናገሩ

AMN- ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም

የማደግ ዕድላችን በእጃችን ነው፣ ኢትዮጵያ ያላት አቅም ግዙፍ ነው ሲሉ የቀድሞ አመራር አቶ ጁነዲን ሳዶ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ከቀድሞ እና በሥራ ላይ ካሉ የመንግስት አመራሮች ጋር ባሌ በሚገኘው በሶፍኡመር ዋሻ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የቀድሞ አመራር አቶ ጁነዲን ሳዶ፣ ያለን አቅም ግዙፍ ነው፣ የማደግ ዕድላችን በእጃችን ነው ያለው ያሉ ሲሆን፤ ስለ ትራንስፎርሜሽን ማውራት ከጀመርን 20 ዓመት ገደማ ይሆናል፣ ነገር ግን ተጨባጭ ነገር መሥራት አቅቶን ተጠላልፈን ቁጭ ብለናል ብለዋል፡፡

የባሌ አካባቢ ታሪክን እንደሚያውቁት የተናገሩት አቶ ጁነዲን፤ የዋሻውን ሥነ-ምህዳራዊ አፈጣጠርን ጭምር እንደሚያውቁ ገልጸዋል፡፡

“ሶፍ ዑመር” የምትባል የገበያ መንደር እንደነበረች የገለፁት አቶ ጁነዲን፤ ይህ ድንቅ የሆነ አካባቢ ከአግሮ ኢኮሎጂው፣ ከታሪክ እና ከቱሪዝም እንዲሁም ከማዕድን አንፃርም ከፍተኛ ሀብቶች እንዳሉት ነው የገለጹት፡፡

ነገር ግን በትግራይ፣ ወለጋ እና ሻኪሶ አካባቢ በማዕድን ሀብት የተሻለ ጥናት እንደተሰራው ሁሉ በባሌ አካባቢ አለመሰራቱን ጠቁመዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራርነት የመጣው አሰራር ግን የባለሙያውንም፣ የአመራሩንም የሀገሪቱንም ህዝብ ዓይን የከፈተ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ሥልጣንን ማዕከል በማድረግ ቁጭ ብለናል ያሉት አቶ ጁነዲን፤ ልማት እናምጣ ከተባለ ግን የልማት ዕድሉ አለ በማለት ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ቻይና እና ደቡብ ምሥራቅ እስያን ጨምሮ ከብዙ ሀገሮች የመማር ዕድሉ እንዳለም አንስተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ዘመን የዲጂታላይዜሽን ዘመን የመስፈኑ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኛ ሀገር እምቅ አቅም ያለው እርሻ ላይ ነው በማለትም፣ እርሻው ገና እንዳልተበላበት አቶ ጁነዲን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review