ተመራማሪዎች ከጥልቅ ውቂያኖስ ውስጥ ለመጠጥነት የሚውል ውሀ አገኙ

You are currently viewing ተመራማሪዎች ከጥልቅ ውቂያኖስ ውስጥ ለመጠጥነት የሚውል ውሀ አገኙ

AMN – ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም

የምድር 70 በመቶ ክፍል ውሀ እንደሆነ ቢነገርም ለመጠጥነት የሚውለው ግን 2 በመቶ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውስጥ 1 በመቶ ብቻ የሚሆነው ከሀይቅ እና ወንዞች የሚመረት በመሬት የላይኛው ክፍል የሚገኝ ነው።

ከ50 አመት በፊት በአትላንቲክ ውቂያኖስ ጥልቅ ላይ ማዕድን ለመፈልግ በተቆፈረ ስፍራ ለመጠጥነት የሚያገለግል ውሀ መገኘቱ ተሰምቷል።

በዚህ ትልቅ የውቂያኖስ ክፍል ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ናሙናዎችን በመውሰድ ምርምር ሲያደርጉ የቆዩት ተመራማሪዎች፤ ለመጠጥነት የሚውል ውሀ በጨዋማው የባህር ክፍል ማግኘታቸውን ነው ይፋ ያደረጉት።

በተለምዶ ከሚገኘው የመጠጥ ውሀ አይነት ጋር ለማመሳከር በመጪዎቹ ወራት 50 ሺህ ሊትር የሚለካ ውሀ ወደ ቤተ ሙከራ በመውሰድ ምርምር እንደሚደረግበት አሶሼትድ ፕረስ አስነብቧል።

ከዚህ ባለፈም ባልተለመደ ሁኔታ በውቂያኖስ ውስጥ የተገኘው የመጠጥ ውሀን ምንጭ ለማጣራት እንዲሁም ከባህሩ ጋር ሳይቀላቀል በምን አይነት መንገድ ማውጣት ይቻላል በሚለው ዙሪያ ምርምሮች ቀጥለዋል።

25 ሚሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት በውቂያኖስ ውስጥ ውሀን ፍለጋ እና ምርምር፤ በአሜሪካ መንግስት የሳይንስ ፋውንዴሽን እና በሌሎች ውሀ ላይ በሚሰሩ አለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገለት ነው።

አሁን ባለው የምርምር ውጤት ደረጃም በውቂያኖስ ውስጥ የሚገኘው ንጹህ ውሀ ኒውዮርክን የመሳሰሉ ግዙፍ ከተሞችን የውሀ ፍላጎት ለ800 አመታት ማሟላት የሚያስችል እንደሆነ ነው የተዘገበው።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ሲመናመን በአንጻሩ የሰው ልጅ የውሀ ፍላጎት በ40 በመቶ ይጨምራል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review