የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ከማስፋፋት ባሻገር በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር አቅዳ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከ2025 የአለም ባንክ እና የአለም የገንዘብ ድርጅት አመታዊ ስብሰባዎች ጎን ለጎን፣ በጤና ስራ አመራሮች ጥምረት ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡
የዉይይት መድረኩ በአለም ባንክ ፕሬዝዳንት እና በአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር የተዘጋጀ ሲሆን የዉይይቱ ዋና አላማም አለም አቀፍ መሪዎችን በማሰባሰብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በዉይይቱ ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያ የማይበገር እና በራሱ የሚተማመን የጤና ስርዓት ለመገንባት ባላት ስትራቴጂያዊ ራዕይ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ሽፋንን በማስፋፋት ረገድ አመርቂ መሻሻል ማሳየቷን የገለጹት ሚኒስትሩ ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች በጤና ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዉይይቱ ወቅት የኢትዮጵያን የጤና ዘርፍ ለመቀየር የሚያግዙ አራት ስትራቴጂያዊ እቅዶችን አቅርበዋል።
ስትራቴጂያዊ እቅዶቹም የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሽፋንን ማስፋፋት፡ ኢትዮጵያን በጤና ጥበቃ ዙሪያ የቀጣናዉ መሪ አድርጎ መሾም፤ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት የጤና ወጪ ውጤታማነትን በ 20 በመቶ ማሻሻል እና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማጠናከር መሆኑን አንስተዋል፡