ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ በተገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ

You are currently viewing ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ በተገኙ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ርምጃ ተወሰደ

AMN – ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም

በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከነዳጅ ሽያጭ እና ማከፋፈል ሂደት ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥ ድርጊት በፈጸሙ ማደያዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አስታወቀ።

በዚህም መሠረት፤ ዲጂታል ሽያጫቸው ከ50 በመቶ በታች በሆኑ 354 የነዳጅ ማደያዎች ላይ በአዋጁ መሠረት ርምጃ መወሰዱን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ በቀለች ኩማ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዲጂታል ሽያጫቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሥድስት የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ላይ በአዋጁ መሠረት ለሁለት ወራት የነዳጅ ጭነት እንዳይደረግላቸው መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የዲጂታል ሽያጫቸው መጠነኛ በሆኑ ሰባት ኩባንያዎች ላይ በአዋጁ መሰረት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አንድ ማደያ ነዳጅ በበርሜል በመቅዳት የጥቁር ገበያ ሽያጭ ለማከናወን ሲንቀሳቀስ በመያዙ ለሥድስት ወራት ከነዳጅ ትስስር መታገዱንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል መዳረሻው አዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ በሚገኝ ማደያ የነበረ አውቶ ቦቴ መዳረሻውን በመቀየር ወደ ሌላ ከተማ በመጓዙ ለሥድስት ወራት ከነዳጅ ትስስር እንዲታገድ መደረጉን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ በዲላ ከተማ የሚገኝ አንድ ማደያም መንግሥት ካወጣው ዋጋ በላይ በመሸጡ የነዳጅ አቅርቦት እንዳያገኝ በሲስተም ሎክ መደረጉን ነው ያረጋገጡት።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭትና ግብይት ቁጥጥር ሥርዓቱ ፈጣን፣ አስተማማኝና ጥራት ያለው እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን ማጠናከሩንም አስታውቋል።

ሁሉም የነዳጅ አከፋፋዮችና ማደያዎች ህግን ተከትለው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review