ሪያል ማድሪድ ከ ጁቬንቱስ፡- የሃያላኑ ፍልሚያ

You are currently viewing ሪያል ማድሪድ ከ ጁቬንቱስ፡- የሃያላኑ ፍልሚያ

AMN-ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የ3ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ሪያል ማድሪድ በሜዳው ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ጁቬንቱስን ያስተናግዳል፡፡

ሁለቱ የአውሮፓ ሃያላን በእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ከህሊና የማይጠፉ አስደናቂ ፉክክሮችን አሳይተዋል፡፡ በአጠቃላይ 22 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ጁቬንቱስ 10 ጨዋታ በማሸነፍ መጠነኛ የበላይነት አለው፡፡

የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ የዛሬ ተጋጣሚው ላይ ዘጠኝ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ የስፔኑ ክለብ በተለይ ከ1998 በኋላ ጁቬንቱስ ላይ የበላይነቱን ወስዷል፡፡

እ ኤ አ 1998 እና 2017 ላይ ለፍፃሜ ሲገናኙ አሸናፊ የሆነው ሪያል ማድሪድ ነው፡፡ 2018 ላይ ያደረጉት የሩብ ፍፃሜ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች በርካታ ድራማዎችን እና ውዝግቦችን አሳይቶ በማድሪድ አጠቃላይ 4ለ3 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

በተለይ በቱሪን በተደረገው ጨዋታ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያስቆጠራት ’’የመቀስ ምት’’ ግብ መዘንጋት ይከብዳል፡፡ በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ላይ ደግሞ ጂያን ሉጂ ቡፎን በቀይ ካርድ የወጣበት አጋጣሚ አይረሳም፡፡ ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ዘመን አይሽሬ ፉክክር በኋላ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ይጫወታሉ፡፡

ሁሌም ውጥረት የሚበዛበት የሪያል ማድሪድ እና ጁቬንቱስ ጨዋታ በ21 ግንኙነት ስምንት ቀይ ካርዶች ተመዘዋል፡፡ ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት የሚጀምረውም ጨዋታ ሞቅ ያለ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሞናኮ ከ ቶተንሃም ፣ ባየርን ሙኒክ ከ ክለብ ብሩጅ ፣ ቼልሲ ከ አያክስ ፣ ስፖርቲንግ ከ ማርሴይ እንዲሁም አታላንታ ከ ስላቪያ ፕራግ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ናቸው፡፡

አትሌቲክ ቢልባኦ ከ ካራባግ ፤ ጋላታሳራይ ከ ቦዶ ግሊምት ምሽት 1፡45 ላይ ጨዋታቸውን ይጀምራሉ፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review