በአዲስ አበባ አዳዲስ የተገነቡ ሲኒማ ቤቶች ከዚህ ቀደም በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የነበረውን ችግር የሚቀርፉ ናቸው ሲል አርቲስት ተሻለ ወርቁ ተናግሯል፡፡
በተለያየ ልፋት ውስጥ ሆነው የሚሰሩ ትያትር እና ፊልሞች በማሳያ ቦታ እጥረት ሥራው በወረፋ ይቀርብ እንደነበር ያነሳው አርቲስቱ፣ ጥቅምት ላይ ተሰርቶ ያለቀ ፊልም በወረፋ ምክንያት ሚያዚያ ላይ ይታይ እንደነበር የራሱን ተሞክሮ አጋርቶናል ፡፡
በተመሳሳይ ሌሎችም ባለሙያዎች እንደዚህ አይነት ፈተና ይገጥማቸው እንደነበር እና ይህም ለኪነ-ጥበብ ባለሞያው ከባድ ችግር እንደነበር ነው ተሻለ ወርቁ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበረው ቆይታ የገለፀው ፡፡
አንድ ባለሙያ የፃፈው እና የሰራው ነገር ወቅታዊ ጉዳዮች በውስጡ ሊኖሩ ስለሚችሉ ቶሎ ወደ ተደራሲያኑ እንዲደርስለት ይፈልጋል ያለው ባለሙያው፤ በሰዓቱ ካልታየ ሊያልፍበት እንደሚችልም ነው ተናገረው፡፡

ብዙ ተለፍቶበትና ተደክሞበት የተሰራ ሥራ በወቅቱ ሳይቀርብ ሲቀር ትልቅ ሙያዊ ኪሳራ መሆኑን በመግለፅም፣ ለዚህም የሲኒማ ቤት እጥረት የዘርፉ ትልቁ ፈተና እንደነበር አንስቷል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር በከተማ ያለውን የቲያትር እና የፊልም ማሳያና መስሪያ ቦታዎች አጥረት ለመቅረፍ ዘመናዊ ኮምፕሌክሶችን መገንባቱ ባለሞያው አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች ይዞ እንዲቀርብ ዕድል የሚሰጥ ነው ሲል ተናግሯል፡፡
አሁን ላይ የተመረቁት ኮምፕሌክሶች ከኮቪድ 19 ወዲህ ተቀዛቅዞ ለነበረው የሲኒማ ኢንዱስትሪ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ያነሳው አርቲስቱ፤ በአዳዲስ ሲኒማ ቤቶች ምን ይዘን እንቅረብ በሚለው ጉዳይ ከባልደረቦቹ ጋር እየመከረ መሆኑንም አንስቷል፡፡
የኢትዮጵያ የፊልም ተመልካቾች እጅግ ትዕግስተኞች መሆናቸውን የጠቆመው ባለሙያው፣ ተመልካቹ የሀገሩን ፊልም ከመውደዱም ባለፈ የነበሩትን ችግሮች ተቋቁሞ የጥበብ ስራዎችን ሲመለከት መቆየቱን እና አሁን ላይ ግን ለተመልካችም እፎይታን የሚሰጡ መመለከቻ ቦታዎች መሰራታቸውን ነው የገለፀው ፡፡
ከአዳዲስ ሲኒማ ቤቶች መከፈት በተጨማሪ የአዲስ አበባ ውብና ማራኪ ገፅታ መላበስ ለፊልም ቀረፃ ስራዎች ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም ነው አርቲስት ተሻለ ወርቁ የገለፀው ፡፡
በታምራት ቢሻው