ፈጣኖቹ አትሌቶች የሚፋጠጡባት የቫሌንሲያ ማራቶን

You are currently viewing ፈጣኖቹ አትሌቶች የሚፋጠጡባት የቫሌንሲያ ማራቶን

AMN-ጥቅምት 12/2018 ዓ.ም

45ኛው የቫሌንሲያ ማራቶን በፈረንጆቹ አቆጣጠር ታህሳስ 7 2025 በስፔን ቫሌንሲያ እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ የዘንድሮ ውድድር ከሌላው ጊዜ በተለየ ፈጣን አትሌቶች የሚፋጠጡበት ነው፡፡

በወንዶች ኢትዮጵያዊው ሲሳይ ለማ ይጠበቃል፡፡ ሲሳይ የ2023ቱን የቫሌንሲያ ማራቶን ሲያሸንፍ የገባበት 2፡01፡48 የዓለማችን የምንጊዜውም አራተኛው ፈጣን ሰዓት እንዲሁም የቫሌንሲያ ማራቶን ክብረወሰን ነው፡፡

ሲሳይ ለማ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የተካሄደውን የቦስተን ማራቶን ማቋረጡ አይዘነጋም፡፡ በጉዳት ምክንያት ከ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ውጭ የሆነው ሲሳይ ለማ የቫሌንሲያን ማራቶን ለማሸነፍ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ይጠቁማል፡፡

አራት አትሌቶች 2፡05 ሰዓት በታች ይዘው ቫሌንሲያ ላይ ይሮጣሉ፡፡ ኃይለማሪያም ኪሮስ አንዱ ነው፡፡ የ2025ቱን የሲድኒ ማራቶን ያሸነፈው ኃይለማሪያም 2፡04፡35 ሰዓት ይዞ ቫሌንሲያ ላይ የሚሮጥ ሁለተኛው ፈጣን አትሌት ነው፡፡ ኬንያዊ ሂላሪ ኪፕኮች፣ ጀርመናዊያኑ ሳሙኤል ፍትዊ እና አማኑኤል ፔጥሮስ ሌሎች ፈጣን ሰዓት ያላቸው አትሌቶች ናቸው፡፡

የሴቶቹን አሸናፊነት ግምት ኬንያ ወስዳለች፡፡ በቅርቡ በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ያሸነፈችው ፔሬዝ ጄፕቺርቺር ከቶኪዮ መልስ ትጠበቃለች፡፡ የኒው ዮርክ ፣ ቦስተን እና ለንደን ማራቶኖችን ያሸነፈችው ጄፕቺርቺር ቫሌንሲያ ላይ ቀዳሚውን ግምት ያገኘች አትሌት ናት፡፡

የቦታው ፈጣን ሰዓት ባለቤት አማኔ በሪሶም የአሸናፊነት ግምት አግኝታለች፡፡ የ2023ቱ የቡዳፔስቱ ዓለም ሻምፒዮና አሸናፊዋ አማኔ ቫሌንሲያ ላይ የምትጠበቅ አትሌት ናት፡፡ የ2022ቱን የቫሌንሲያ ማራቶን ስታሸንፍ የገባበችበት ሁለት 2፡14፡58 የቦታው ክብረወሰን ነው፡፡

አማኔ በ2023ቱ የቦስተን ማራቶን ሶስተኛ እንዲሁም በፓሪስ ኦሊምፒክ አምስተኛ ደረጃን ይዛ መጨረሷ ይታወሳል፡፡ ኬንያዊቷ ጆይስሊን ጄፕኮስጌ፣ አማሪካዊቷ ኬይራ ዲአማቶ፣ ኢትዮጵያዊቷ ፍቅርተ ወረታም ቢሆኑ ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡

የዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከሰጣቸው የጎዳና ላይ ውድድሮች አንዱ የሆነው የቫሌንሲያ ማራቶን፤ አትሌቶች ፈጣን ሰዓት ከሚያስመዘግቡባቸው ኮርሶች አንዱ መሆኑ አይዘነጋም፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review