ኢትዮጵያ የአባልነት ድርድሩን በካሜሩን ያውንዴ በፈረንጆቹ መጋቢት 2026 በሚካሄደው የዓለም የንግድ ድርጅት 14ኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ ወቅት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ገለጹ።
ገዥው ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በዓለም የንግድ ድርጅትና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ኒል ቤክ ጋር የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት ድርድርን በተመለከተ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የኢትዮጵያን የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነት አስመልክቶ የተካሄደውን የስድስተኛ የስራ ቡድን ስብሰባ ውጤት እና ከስብሰባው በኋላ የተከናወኑ ቁልፍ ማሻሻያዎችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአባልነት ድርድሩን በካሜሩን ያውንዴ በፈረንጆቹ መጋቢት 2026 በሚካሄደው የዓለም የንግድ ድርጅት 14ኛ የሚኒስትሮች ጉባዔ ወቅት ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኗን ነው የገለጹት።
የአባልነት ሂደቱ በተቀመጠ የጊዜ ገደብ እና በተጨባጭ ስራ፣ በትጋት እና የንግድን መዋቅራዊ ለውጥ የማምጣት አቅምን በሚገነዘብ አመራር መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶችን ለማሟላት ያላትንም ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከአባል ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የምታገኘውን ከፍተኛ ድጋፍ ጠቅሰው፤ አሜሪካም በዚህ ረገድ የተጠናከረ ድጋፍ እንድታደርግ ነው የጠየቁት።
በዓለም የንግድ ድርጅት እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች የአሜሪካ ረዳት የንግድ ተወካይ ኒል ቤክ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን እየሰራችው ያለውን ስራ አድንቀው አሜሪካ ተገቢውን ተሳትፎ እንደምታደርግ ማስታወቃቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን ማሟላት ያለባትን መስፈርት በግልፀኝነት ለማሳወቅም እንደሚሰሩም ተናግረዋል።