በግብርናው ዘርፍ ብዛት ፣ ጥራትና ቀጣይነት ያለው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ ተገለፀ።
በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ፣ ረቂቅ አዋጁ የግብርና ሴክተሩን በብዙ መልኩ የሚቀይር ነው ብለዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከዚህ ቀደም ውይይት እና የአስረጂ መድረክ የተካሄደ ሲሆን የተካሄደው ውይይት ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት አማካሪው አቶ ተፈራ ዘርአይ በበኩላቸው ፣ የረቂቅ አዋጁን ይዘት ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።
ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት፣ አስተዳደርና ልማት እንዲሁም በተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ያለውን የተደራሽነት፣ የጥራት፣ የአቅም እና የአፈጻጸም ውስንነትን ለመቅረፍ የሚያስችል እንደሆነ ተጠቁሟል።
ረቂቅ አዋጁ ዳብሮ ከፀደቀ ለህብረተሰቡ የኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ በግብርና ስራ የተሰማሩ ባለሀብቶች፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ሌሎችም ሌሎችም መስራት የሚችሉ ባለድርሻ አካላት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ህጋዊ ማዕቀፍ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከፌዴራል ፣ ከክልሎች እንዲሁም ከሙያ ማኅበራት የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን በረቂቅ አዋጁ ላይ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ሀሳቦችና የግልፅነት ጥያቄዎችን አንስተው በቋሚ ኮሚቴ አባላትና የአስረጂ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በይታያል አጥናፉ