ለሀገርና ለህዝብ ሠላም የተጀመረውን የህዝብና የፀጥታ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር አስተማማኝ ሠላም ልንፈጥር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አሰተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ጥሪ አቀረቡ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አሰተዳደር ቢሮ ለሠላም ሠራዊት አባላት የምስጋናና እውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመዲናዋ በ2017 እና በ2018 መስከረም ወር የተከበሩ ሕዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች በስኬትና በድምቀት እንዲከናወኑ የከተማዋ የሠላም ሠራዊትና የተለያዩ የፀጥታ አካላት የስራ ውጤት መሆኑን የተናገሩት የአዲስ አበባ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ ለዚህ ውጤታማና ሀገራዊ ሀላፊነታችሁ ምስጋና ይገባችኋል ብለዋል።

አሁንም ሆነ ነገ የኢትዮጵያ ጠላቶች አይተኙም ያሉት ኃላፊዋ፤ ለእነዚህ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች እኛ በትጋትና በቅንጅት በመስራት ጠላትን ማሳፈር፣ የከተማችንና የሀገራችንን ሠላም አስተማማኝ ማድረግ ይገባናል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው፤ የአዲስ አበባ የሠላም ሠራዊት አባላት ከተማዋ 24 ሠዓት በመስራት ለፖሊስ አጋዥና የመረጃ ምንጭ በመሆን ትልቅ ስራ በመስራት ውጤት አምጥተናል ብለዋል።
ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣታቸው ለሰላም ሰራዊቱ ምስጋና ያቀረቡት ኮሚሸነር ጌቱ፤ ለቀጣይም ፖሊስ የጀመረውን የህዝብ ተሳትፎና ከሠላም ሠራዊቱ ጋር በአብሮነት የመስራት ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራን ጨምሮ የከተማ ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች፤ የከተማዋ የሠላም ሠራዊት አባላት የታደሙ ሲሆን ክፍለ ከተሞችና የሠላም ሠራዊት አባላት እውቅናና ምስጋና ተበርክቷል።
በአንዋር አህመድ