የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ ልዩ ኢኮኖሚ ዞንን ጎብኝተዋል።
በመርሃ ግብሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ እንዲሁም የምክር ቤቱ አባላት ተገኝተዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለጎብኝዎቹ በሰጡት ማብራሪያ፥ አምራች ኢንዱስትሪው በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ሰባት ዓመታት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በየደረጃው ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን ማነቆዎች በጉልህ መፍታት ማስቻሉን ተናግረዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እየተፈቱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲኖረው ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
መንግስት የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየሰራ ስለመሆኑ በመጥቀስ፥ ውጤቶችን የማጠናከርና ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ እየተሰጠ እንደሚገኝ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምክር ቤቱ አመራሮች እና አባላት በቀጣይም የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።