ሀገራዊ ምክክር፤ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በህዝቦች መካከል መተማመን ለመፍጠር እና ምክክርን ባህል ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንደለው ተገለፀ

You are currently viewing ሀገራዊ ምክክር፤ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በህዝቦች መካከል መተማመን ለመፍጠር እና ምክክርን ባህል ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንደለው ተገለፀ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN – ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም

እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክሮችን ማድረግ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር አጋዥ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዩናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽነር ዩናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው ሀገራዊ ምክክር፤ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በህዝቦች መካከል መተማመንን ለመፍጠር፣ ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት እና እንደ ሀገር ምክክርን ባህል ለማድረግ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባትንና አንድነትን ለመፍጠር ብሎም መተማመንና ተቀራርቦ መስራትን ለማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ ማህበራዊ እሴቶችን ለማደስ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚያግዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ ጠቅሰዋል፡፡

ኮሚሽኑ እስካሁን በአጀንዳ ማሰባሰብ እና ልየታ ሥራ ብዙ ርቀት የተጓዘ ሲሆን በተለየዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና በውጪ ሀገራት ውይይት በማድረግ አጀንዳ ሲሰበሰብ መቆየቱን ኮሚሽነር ዩናስ አዳዬ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በካናዳ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በእንግሊዝና ስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በማወያየት የአጀንዳ ልየታ ሥራ መከናወኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ በውይይቱ ከሀገራቸው የወጡበትን ምክንያት መስማት እንደ አንድ ግብዓት የሚወሰድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሰሞኑን በትግራይ ክልል በነበረው ቆይታ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ከምሁራኖች እና ከህዝቡ ጋር ባደረገው ውይይት በቀጣይ ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን መገንዘብ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሠላምን በማጽናት የሚከባበርና የሚተማመን ትውልድን ለመፍጠር ብሎም አንድነትንና መግባባትን ለማስፈን ምክክሩ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የገለፁት ኮምሽነሩ፤ ምክክሩ ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል አዎንታዊ ሚና እንዳለው እና ህዝቡም ለስኬቱ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያን ሠላማዊ፣ የበለፀገችና ሁሌም በከፍታ ላይ የምትጓዝ ሀገር ለማድረግ የሚዲያ አካላትን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች የድርሻቸውን እንዲወጡ ኮምሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review