11ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋጽኦ የምታጸናበት መሆኑን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለፁ

You are currently viewing 11ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋጽኦ የምታጸናበት መሆኑን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለፁ
  • Post category:አፍሪካ

AMN – ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም

11ኛው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋጽኦ የምታጸናበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

ከጥቅምት 14 እስከ 16/2018 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው 11ኛው ጣና ፎረም በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ጨምሮ የአፍሪካ ሀገራት፣ የዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። የጣና ፎረም “አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ የደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ለሶስት ቀናት የሚመክር ይሆናል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው እንደገለጹት፥ የጣና ፎረም በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ በመምከር መፍትሔ አመላካች ምክረ ሃሳቦች የሚቀርቡበት አህጉራዊ መድረክ ነው ብለዋል። በፎረሙ ላይ የመንግስት አካላት፣ሚኒስትሮች፣አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል።

“አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ መካሄድ የጀመረው የዘንድሮው የጣና ፎረም አፍሪካ በተለዋዋጭ የዓለም ሁኔታ የሚኖራትን ሚና እንደሚዳስስ አንስተዋል።

ወቅታዊው የዓለም ሁኔታ የፖለቲካ ፉክክር እየከረረና የባለብዙ ወገን ዓለም አቀፍ ትብብር እየላሉ የመጡበት መሆኑን አስረድተዋል። በጣና ፎረም አፍሪካ ውጥረት በተሞላበት ዓለም አቀፍ ሁኔታ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ያሏትን መፍትሔዎች እንደምታራምድ አብራርተዋል።

የጣና ፎረም ትኩረት አፍሪካዊ መፍትሔዎች ላይ ነው ያሉት አምባሳደር ነቢያት፥ በዚህም ከአፍሪካውያን የመነጩ የሰላምና ደኅንነት የመፍትሔ ሃሳቦች የሚንሸራሸሩበት መድረክ ነው ብለዋል። በመድረኩም ለአፍሪካውያን የፖሊሲ አውጪዎች ምክረ ሃሳብ የሚሆኑ ሀሳቦች የሚወጡበት መሆኑንም ገልጸዋል።

ለ11ኛ ጊዜ በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ የሚካሄደው የጣና ፎረም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ያላትን የላቀ አስተዋጽኦ የምታጸናበት መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪካ ሀገራት መሪዎችና ተሳታፊ ሙያተኞች በአፍሪካ የደኅንነት ጉዳዮችና በአፍሪካዊ መፍትሔዎች ልምድና ዕውቀታቸውን የሚያካፍሉበት ዝግጅትም ተጠባቂ የፎረሙ የመርሃ ግብር አካል ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review