ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ መፈጸማቸው የተረጋገጡ 785 ነጋዴዎች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው ሕጋዊ ርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ንግድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊቁ በነበሩ በሕገ ወጥ ንግድ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እና የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በዚህም መሠረት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከዋጋ ጭማሪና ከሕገ ወጥ ንግድ አንፃር በተስተዋሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ ርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።
ለአብነትም በ780 ነጋዴዎች ላይ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ የንግድ ፈቃድ እገዳና ስረዛ እንዲሁም በአምሥት ነጋዴዎች ላይ በሕግ አግባብ የእስራት ርምጃዎች መወሰዳቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ቅጣት ርምጃ መውሰድ መቻሉንም አስታውቀዋል።
በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ሊታዩ የሚችሉ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ያለመ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱንም አውስተዋል።
በዚህም መንግሥት ያደረገውን የደመወዝ ማስተካከያ ብሎም በዓላትን ሽፋን በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይኖር የተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ መሠራቱን እና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
በመሆኑም በጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ርምጃ እንዲወሰድ ለሁሉም የክልልና ከተማ አሥተዳደሮች የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች አቅጣጫ ተሰጥቶ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ነው ያረጋገጡት።
በየደረጃው ያሉ አካላት የገበያ ማረጋጋትና የሕገ ወጥ ንግድ ግብረ ኃይል አቋቁመው እየሠሩ መሆኑ ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ መንግሥት ባስቀመጠው ሕጋዊ መንገድ ብቻ ሥራውን እንዲከውን፤ ሕብረተሰቡም ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ሲመለከት ጥቆማ በመስጠት ለፍትሐዊ ንግድ እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።