”ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” የተሰኘ የጉብኝት መርሃ-ግብር ሊካሔድ ነው

You are currently viewing ”ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” የተሰኘ የጉብኝት መርሃ-ግብር ሊካሔድ ነው

AMN – ጥቅምት 14/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ፣ ብዝሃ ሀብቷን ለማሳየትና ብሄራዊ ኩራትን ለማጎልበት እድል የሚፈጥር ”ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” የተሰኘ መርሃ ግብር ሊካሄድ መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ገለጹ።

መርሀ ግብሩ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሔድ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ (ዶ/ር) ሀገራዊ የጉብኝት መርሃ ግብሩን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

”ጉዞ ወደ ሀገር ቤት” ከኢትዮጵያ ወደ የተለያዩ ዓለም ሀገራት በጉዲፈቻ የሄዱ ህጻናት ሀገራቸውን ባህላቸውንና ማንነታቸውን እንዲያውቁ ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ትስስር እንዲያጠናክሩና ቀጣይነት ያለው ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያግዝ ስለመሆኑም አብራርተዋል።

ይሄው ለሰባት ቀናት የሚካሔደው የጉብኝት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ያላትን ብዝሃ ሀብት ለማስተዋወቅና ብሄራዊ ኩራትን ለማጎልበት እድል የሚፈጥር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተጨማሪም የውጭ ጎብኝዎችን ለመሳብ እና አማራጭ የጉብኝት መርሃ ግብርን ለማዘጋጀት ዓይነተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ በበኩላቸው፤ መርሀ ግብሩ በጉዲፈቻ ባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን የህይወት ጥያቄ መልስ የሚያገኙበትን እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በተለይ ትውልደ ኢትዮጵያን በቱሪዝም፣ በንግድ በኢንቨስትመንት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም ገልፀዋል።

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በመዲናዋ የሚገኙ የተመረጡ የቱሪዝም መስህቦችን በማስጎብኘት በኩል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

እንግዶች ያማረ ቆይታ እንዲኖራቸው እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

መርሀ ግብሩ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሔድ ስለመሆኑም ተገልጿል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review