ኢትዮጵያ ያሏትን የተደበቁ ተፈጥሯዊ ሀብቶች አውጥቶ በመጠቀም መንግስት ጠንካራ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በኮይሻ ግድብ አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት በኮይሻ ለአራተኛ ጊዜ እንደመጡ የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኮይሻ ከግድብነት ባለፈ በታደለው የሚደንቅ ተፈጥሯዊ ጸጋ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን ተናግረዋል ።

ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ለቱሪስቶች መገልገያ እንዲሆኑ ታስበው ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ እንደሚገኙ አንስተዋል።
አክለውም ከ2ሺህ 800 በላይ ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጨው የኮይሻ ግድብ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉ የለውጡ መንግስት የታደገው ፕሮጀክት መሆኑን ነው ያመላከቱት ።
ሀገሪቱ ያላትን ፀጋ አውጥቶ የመጠቀም ልምምድ እያደገ መምጣት የተዘነጉ እና የተረሱ ስፍራዎችን ወደ ኢኮኖሚያዊ አቅምነት የመቀየር ተግባር እንዲዳብር ስለማድረጉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ።
ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ ሀላላ ኬላ እና የኮይሻ ግድብ መሰናሰል ለቱሪዝም ፍሰቱ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርም ተመላክቷል።
በዳዊት በሪሁን