ከአንድ ግለሰብ ስልክ ቀምቶ የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ በመግባት ሊያመልጥ የነበረ ተጠርጣሪ ከ5 ሰዓታት ቆይታ በኋላ ከነ ኤግዚቢቱ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።
ተጠርጣሪው የቅሚያ ወንጀሉን ፈጽሞ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ በመግባት ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር የዋለው ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ/ም በየካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 አቤቤ ሱቅ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው።
ተጠርጣሪው የግል ተበዳይ ከባንክ ብር አውጥተው ሲወጡ ጠብቆ የዋጋ ግምቱ 120 ሺ ብር የሚያወጣ sumsung altra si25 ስማርት ስልክ በመንጠቅ በአካባቢው ወደሚገኝ የቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ገብቷል።
የወንጀል ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ የግል ተበዳይ የይድረሱልኝ ጥሪ በማሠማታቸው የአካባቢው ህብረተሰብ እና ፖሊስ ወዲያው ቦታው ላይ በመድረስ ተጠርጣሪው በገባበት የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ተከታትሎ በመግባት ሊያወጡት መቻላቸውን የየካ ክፍለ ከተ ማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ከቱቦው ውስጥ ሲወጣ ስልኩን ትቶ የወጣ ቢሆንም ፖሊስ ተጠርጣሪውን በድጋሚ ወደ ቱቦው ውስጥ ይዞ በመግባት ስልኩን ከጣለበት ውሃ ውስጥ እንዲያወጣው ማደረጉን የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል።
በእንደዚህ ዓይነት የወንጀል ተግባር ላይ የሚሰማሩ ወንጀል ፈጻሚዎች ከህግ እንደማያመልጡ አውቀው ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል።