ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉ የተለያዩ ችግሮች መንግስት ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከማቀድ፣ ከማስፈፀም እና ለአገልግሎት ከማብቃት እንዳላስቆሙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በኮይሻ ግድብ የ2018 ዓ.ም የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ላይ ባደረጉት ንግግር መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የልማት ስራዎች ኢትዮጵያን ለማወቅ እና አቅሟን ለመረዳት እድል እንደፈጠረላቸው ነው የገለፁት።

በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች በሌላ የአፍሪካ ሀገር ቢከሰቱ ኑሮ ከልማት ስራ ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ቢሆንም ነገር ግን መንግስት ችግሮች ሳይወስኑት ለሀገር የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን በማቀድ እና በማስፈጸም ያለው አቅም የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል ።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን መምጣት ለመሞት ተቃርበው የነበሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች እንዲነሱ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከውጭ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ለመገንባት ታቅዶ የተጀመረ ቢሆንም የታሰበው ድጋፍ ባለመገኘቱ ግንባታው ቆሞ እንደነበር አስታውሰዋል ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኃላ ባደረጉት አጠቃላይ የፕሮጀክት ግምገማ እንደ ህዳሴ ግድብ በራስ አቅም መፈጸም ይቻላል በሚል ተነሳሽነት እና ቀጥተኛ አመራር አሁን ለሚገኝበት ደረጃ መብቃቱን አብራርተዋል።
ከኃይል ማመንጫ ግድቡ በተጨማሪ በኮይሻ እና ዙሪያው የለሙ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅምን የሚፈጥሩ ቱሪዝምን መሠረት ያደረጉ ልማቶች የተገነቡትም ከዚህ ውሳኔ በኃላ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል ።
በዳዊት በሪሁን