ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የ2018 ዓመተ ምህረት የመጀመሪያ የመቶ ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አካሂደዋል፡፡
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ እንደገለጹት፣ በጆኦ ፖለቲካል ውጥረት እና በአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ እድገት መቀዛቀዝ በሚታይበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች ብለዋል፡፡
ለዚህ አመርቂ ውጤት መመዝገብ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አደም፣ የመጀመሪያው ከለውጡ ወዲህ የእይታ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የአመራር የማስፈፀም አቅም ትጋትና ቁርጠኝነት መፈጠሩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የግሉ ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ እና ትብብር ማደግ ለተመዘገበው የኢኮኖሚ ስኬት ሌላኛው ተጠቃሽ ምክንያት መሆኑንም አቶ አደም ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ በሚፈጠሩለት መድረኮች የሚያነሳቸውን ሀሳቦች መንግስት ተቀብሎ የእቅዱ አካል ማድረግ መቻሉ፣ በኢኮኖሚው እድገት የድርሻውን ለመወጣት በቀርጠኝነት ተነሳስቷል ብለዋል፡፡
የግሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ለኢኮኖሚ እድገትና ብልፅግና ያላቸውን ሚና ለመወጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ ትልቅ ለውጥ ያሳዩ በመሆኑ ለተመዘገበው ውጤት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳደረጉ ነው አቶ አደም የገለጹት፡፡
ህዝቡ በተለየ ሁኔታ የሚያነሳቸውን የኑሮ ውድነት፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ከሰላምና ፀጥታ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን፣ መንግስት በአግባቡ ለማቃለል ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ በመቻሉ፣ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች መምጣታቸውንም አቶ አደም ፋራህ ተናግረዋል፡፡
በአስማረ መኮንን