ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የመሪነት ጥበብን ይጠይቃል ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2ዐ18 ዓ/ም የመጀመሪያ የ1ዐዐ ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ በኮይሻ ግድብ መደረጉን ተከትሎ በጨበራ ጩሩጩራ ብሄራዊ ፓርክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ሚኒስትሮቹ ከምልከታው በኃላ ባካሄዱት ውይይት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳሉት ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ለይቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የመሪነት ጥበብን ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር እየሰጡት ያለው አመራር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሀብቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል አቅምን የማውጣትና የመግለጥ ጥበብና ችሎታ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡
የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ ጥቅም ሳይሰጥ የኖረ መሆኑን ገልፀው፤ በለውጡ የመጀመሪያዎቹ አመታት የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲለማ መደረጉንም አውስተዋል፡፡
ዛሬ ላይ አካባቢውን በመሰረተ ልማት አስተሳስሮ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ በዘላቂነትም ሀብት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ኘሮጀክቱ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከሌላኛው የሀገሪቱ ክልል ህዝቦች ጋር የማስተሳሰር እድል የፈጠረና ድልድይ ሆኖ ያገለገለም ነው ብለዋል፡፡
ፓርኩ ወደፊት ትልቅ እድልን ይዞ እንደሚመጣ የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ የትራንስፖርት አማራጮችን በማስፋት ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን አቅም ለማውጣት፣ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና እንደ ሀገር የኢትዮጵያንም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረውም ገልፀዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው