በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት መርሃግብር ማንችስተር ዩናይትድ ብራይተንን ያስተናግዳል።
ባሳለፍነው ሳምንት ሊቨርፑልን በአንፊልድ የረታው ዩናይትድ ዛሬ በሜዳው ፈታኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል።
በሩበን አሞሪም እየተመራ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ የሊግ ጨዋታ ያሸነፈው ዩናይትድ ጥሩ ተነሳሽነት ላይ ይገኛል።
ዛሬ ከብራይተን የሚገጥመው ፈተና ግን ቀላል አይሆንለትም።
የፋብያን ኸርዝለር ቡድን ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ካደረገው የመጨረሻ ሰባት የሊግ ጨዋታ በስድስቱ አሸንፏል።
ከእነዚህ ድል ውስጥ ለሦስት ተከታታይ ዓመት በኦልድትራፎርድ ያሸነፉበት ይጠቀሳል።
ዩናይትድ በኦልድትራፎርድ የውድድር ዓመቱን በአርሰናል ተሸንፎ ቢጀምርም በርንሌይ ፣ ቼልሲ እና ሰንደርላንድን በመርታት ውጤቱን አስተካክሏል።
በጨዋታው ቡርኖ ፈርናንዴዝ ለዩናይትድ 300ኛ ጨዋታውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአንፊልድ የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው ሀሪ ማጓየር እና ሜሰን ማውንት በጨዋታው መሳተፋቸው እንዳልተረጋገጠ ሩበን አሞሪም አሳውቋል።
ጨዋታው 11 ሰዓት ላይ የሚጀምር ይሆናል።
በተመሳሳይ ሰዓት ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ሰንደርላንድን ሲያስተናግድ ፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ፉልሃምን ይገጥማል።
የዕለቱ መርሃግብር ምሽት ላይም ሲቀጥል 4 ሰዓት ላይ በሊጉ ሦስት ተከታታይ ጨዋታ የተሸነፈው ሊቨርፑል ከሜዳው ውጪ ከብሬንትፎርድ ይጫወታል።
በሸዋንግዛው ግርማ