የቱሪዝሙ አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing የቱሪዝሙ አዲስ ምዕራፍ

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከአፍሪካ ከፍተኛ የቱሪስቶች መዳራሻ እየሆነች መምጣቷን የዓለም የቱሪዝም ባሮ ሜትር መረጃ አመላክቷል

በሳህሉ ብርሃኑ

የቱሪዝም ሴክተሩ የስኬት መዝገብ ሲገለጥ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ፈረንሳይ፣ አሜሪካና ስሎቬንያ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ሆነው ለመጠቀሳቸው በምክንያትነት የሚነሳው የዘርፉን መሰረተ ልማት በአግባቡ በማልማታቸው ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ የወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም ተማራማሪ ማክሲም ሶሽኪን እንደሚሉት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ለቱሪዝም ሴክተሩ የኢንዱስትሪው መሰረት በመሆኑ ቱሪስቶችን የመሳብ እና የማስተናገድ አቅም ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ጠንካራ የቱሪዝም መሠረተ ልማት በማዘጋጀት ረገድ በምሳሌነት የምትጠቀሰውን ስሎቬንያን ነጥለን በመመልከት ምን ስለሰራች በቱሪዝም ሴክተሩ ውጤታማ መሆን ቻለች? ለሚለው ጥያቄ መልስ ስንፈልግ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ቱሪዝሙ የጀርባ አጥንት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዘርፉ ስኬታማነትም የቱሪዝም መዳረሻ አካባቢ ማህበረሰቦችን ከማሳተፍ ጎን ለጎን የመንግስት እና የግል ተቋማት ጠንካራ አጋርነቶች ዋነኛ ምክንያት ሆኖ እናገኘዋለን።

ሀገሪቱ ከዘረፉ ምን እየተጠቀመች ነው? የሚለው ጥያቄ ይመልስልን ዘንድም ጉዳዩን በቁጥራዊ ማስረጃ ወደማስደገፉ እንለፍ፡፡ ስሎቬኒያ እ.ኤ.አ በ2023 ከቱሪዝም 3 ነጥብ 24 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ ያገኘች ሲሆን፣ በዚያኑ ዓመት የቱሪዝም ቀጥተኛ የሀገር ውስጥ ምርት አበርክቶም 3 ነጥብ 33 ሚሊዮን ዩሮ ነበር፤ ይህም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 5 ነጥብ 2 በመቶ ድርሻ እንደነበረው የሀገሪቱ የቱሪዝም መስሪያ ቤት መረጃ ያሳያል፡፡ 

ለንጽጽር ይረዳ ዘንድ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ስናቀና የምናገኘው መረጃ በተቃራኒው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከሣር ሜዳዎች እና ደኖች እስከ ረግረጋማ ቦታዎች፣ ኮረብታዎች እና ሸለቆዎች ድረስ የተለያዩ መልክዓ ምድሮች ያሉት ይህ ቀጠና ከቱሪዝም ሴክተሩ እያገኘ ያለው ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የስታቲስታ ገፀ ድር መረጃን ዋቢ አድርገን ከተመለከትን የቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት ያሳያል ተብሎ በተገመተበት እ.ኤ.አ በ2025 በዘርፉ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሀብት ከ4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የተሻገረ አይደለም፡፡ ይህ ጥቅል መረጃ በቀጣናው ያሉ የ16 ሀገራት እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡

‘ምድረ ቀደምት’ እና የሺህ ዓመታት ታሪክ፣ ባህልና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያም እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በቱሪዝም ዘርፍ ያላት ስኬት ከላይ በማሳያነት ከጠቀስነው የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ሁናቴ የተለየ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን በቱሪዝም ዘርፍ እምቅ አቅም ይኑራት እንጂ፣ ሀገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን ያህል ጥቅም ሳታገኝ ስለመቆየቷ የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት እና መሰረተ ልማትን በማሟላት ትልቅ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። ይህ ጥረት የሀገር ገጽታ ግንባታን ከማጠናከር ባሻገር፣ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ ስለመሆኑ የሚገልፁትም የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ናቸው።

መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን እንደ አንድ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጎ በመውሰድ በተለይም እንደ ‘ገበታ ለሸገር’፣ ‘ገበታ ለሀገር’ እና ‘ገበታ ለትውልድ’ የመሳሰሉ መርሃ ግብሮችን በመተግበር አዳዲስ መስህቦች ወደ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ተቀይረዋል። እነዚህ ፕሮጀክቶች በዋናነት በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የክልል ከተሞች የሚገኙ አካባቢዎችን ለአረንጓዴ ልማት እና ለጎብኚዎች መዝናኛነት በማዘጋጀት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋልም ይላሉ አቶ አለማየሁ ጌታቸው። በተጨማሪም በዘርፉ ያለውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማዘመን፣ የግል ባለሀብቶች በልማቱ እንዲሳተፉ ማበረታታት እና የቱሪዝም ገበያን የማስተዋወቅ ትኩረት ተሰጥቷል።

የቱሪዝም ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን የመሰረተ ልማት አቅርቦት ቁልፍ ስለመሆኑ የሚገልጹት ደግሞ የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) ናቸው። በዚህ ረገድ፣ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችን (እንደ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ) ዘመናዊ ማድረግና የማስፋፊያ ሥራዎችን ማከናወን፣ በተለያዩ ክልሎች ተጨማሪ አውሮፕላን ማረፊያዎችን መገንባት እንዲሁም ወደ ተራራማ እና ቆላማ አካባቢዎች የመንገድ መሠረተ ልማት ማሟላት ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል። የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መስፋፋትና የዓለም አቀፍ የሆቴል ሰንሰለቶችን ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ የጎብኚዎችን ምርጫ ለማርካት እየረዳ ስለመሆኑም የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል፡፡

የቱሪዝም ሚኒስቴር ነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲጎለብቱ እና የቱሪዝም ምርትና አገልግሎት በዓይነትና በመጠን እንዲያድጉ በትኩረት እየሰራበት ካሉ አካባቢዎች መካከል እንደ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ያሉ መዳረሻዎች ተጠቃሽ ናቸው። በሶፍ ዑመር ዋሻ ላይ እየተደረገ ያለውም የተቀናጀ ልማት ለቱሪዝም ዘርፍ የተሰጠውን ትልቅ ስትራቴጂያዊ ትኩረት ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል በመሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን አንስተን እንለፍ፡፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮና የባህል ቅርሶቿን ወደ ዘላቂ የኢኮኖሚ ምንጭነት ለመቀየር በወሰደችው ስልታዊ እርምጃ፣ እንደ ሶፍ ዑመር ዋሻ ያሉ ዓለም አቀፍ እምቅ አቅም ያላቸውን የቱሪዝም መዳረሻዎች በአዲስ መልክ የማልማት እና መሠረተ ልማት የማሟላት ሥራ አጧጡፋለች። ይህ ጥረት ከአፍሪካ ረጅሙና እጅግ አስደናቂ ከሆኑት የከርሰ ምድር ዋሻዎች አንዱ የሆነው የባሌ ሶፍ ዑመር ዋሻን ከዓለም የቱሪዝም ካርታ ላይ ጎላ አድርጎ ለማስቀመጥ ያለመ ነው። እንደ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ አስተያየት ከሆነም መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍን የሀገር ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ምሰሶ ለማድረግ ባስቀመጠው የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ መሠረት፣ በሶፍ ዑመር አካባቢ በርካታ የመሠረተ ልማት እና የአገልግሎት ማሻሻያ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

በአካባቢው እየተሰሩ ካሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች መካከል የመንገድ ግንባታና ማሻሻያ ስራዎች ሲሆኑ፣ ከሮቤ ወደ ሶፍ ዑመር የሚወስደው መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ የማሳደግ ሥራ የአካባቢውን ተደራሽነት ከፍ በማድረግ የጉዞ ጊዜንና ወጪን በእጅጉ ይቀንሳል፤ ይህም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ በአካባቢው የተገነባውና ለሥነ-ምህዳር ተስማሚ በሆነ መንገድ የተነደፈው ሶፍ ዑመር ሎጅ (Luxury Lodge) በአካባቢው ከፍተኛ ደረጃ ያለው መስተንግዶና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። በሌላም በኩል የዋሻውን ስነ-ምህዳር ለመጠበቅና ዓመቱን ሙሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ እንደ የወይብ ወንዝ የጎርፍ መቆጣጠሪያ ፕሮጀክት ያሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ይህ የዋሻውን ሥነ-ምህዳር ከመጠበቅ በተጨማሪ የቱሪዝም አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው።

የሶፍ ዑመርን የተፈጥሮ ውበት፣ የጂኦሎጂካል አፈጣጠር (የኖራ ድንጋይ ምሰሶዎችና አዳራሾች) እና የመንፈሳዊ ቅርስነት (በሙስሊም ቅዱስ ሼክ ሶፍ ዑመር የተሰየመ ቅዱስ ቦታ መሆኑ) ተጣምሮ አካባቢውን ለዓለም በማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ተደርጓል። በአካባቢው ማኅበረሰብ ላይ የተመሠረተ ቱሪዝምን ለማጎልበትም ያስችላል። የሶፍ ዑመርን መሰረተ ልማት ማልማት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ከፍ ያደርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉት በአስደናቂ ብዝሃ መልኩ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝማችን አንዱ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ቀጥሏል።

በመንገድ መሠረተ ልማት ረገድ የሮቤ-ጎሮ-ሶፍ ኡመር-ጊኒር መንገድ የማሻሻያ ፕሮጀክት የኢኮኖሚ ተያያዥነትን ብቻ ሳይሆን እንደሶፍ ዑመር ዋሻ እና የባሌ ተራሮች ወደ መሰሉት ዐበይት የመስህብ ሥፍራዎች ጉዞን የሚያሳልጡ መሆናቸው ተመስክሮላቸዋል።  ድርብ አስፋልት ንጣፍ ባለው ከፍ ያለ ደረጃ የተገነባው መንገድ 29 ኪሎ ሜትር የከተማ እና የገጠር መንገድን የሚያካትት ብሎም ከ12 እስከ 140 ሜትር ርዝመት ያላቸው አምስት ድልድዮች የተሠሩበት ነው። ከአዲስ አበባ ከተማ በስተደቡብ ምስራቅ በ400 ኪሎ ሜትሮች ርቀት የሚገኘው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከ2 ሺህ ኪሎ ሜትር ስኴር በላይ ስፋት ላይ ይገኛል።

ለማሳያ ያህል ከላይ ከተጠቀሱት ቦታዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከጀመረቻቸው የቱሪዝም መዳረሻዎች በርካታ ከተሞች ተነቃቅተዋል፡፡ እንደ ወሊሶና ባህር ዳር ያሉ ከተሞች የወንጪ እና የጣና ሐይቆች መልማታቸውን ተከትሎ የሀገር እና የውጭ ጎብኚዎች መዳረሻ ሆነዋል፡፡ በዚህም የመንግሥት የልማት ጥረቶች ትሩፋቶቻቸውን ማሳየት ስለመጀመራቸውም አቶ አለማየሁ ይገልጻሉ።

የቱሪዝም ባለሙያው አያሌው ሲሳይ (ዶ/ር) በበኩላቸው የቱሪዝም መሠረተ ልማት መሟላት የጎብኚዎችን ቁጥር ይጨምራል ይላሉ። ይህም በቀጥታ በውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ መጨመር ያስከትላል። በቅርቡ በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገበው የገቢ ዕድገት የልማት ሥራዎቹ ውጤት መሆኑን ያመላክታል።

በቱሪዝም ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉት ሥራዎች ውጤታማነታቸውን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች አሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቱሪስት ፍሰት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል። ለምሳሌ፣ የዓለም የቱሪዝም ባሮ ሜትር መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአፍሪካ ሁለተኛ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት ዕድገት አስመዝግባለች። ይህ ዕድገት በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል፤ በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የውጭ ጎብኚዎችን ማስተናገድ መቻሉንና በተለይ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እንዲስፋፋ እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ስለመታየቱ የኮሙኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ጌታቸው ያስረዳሉ።

ቱሪዝም ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ድርሻም ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ ሲሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሴክተሩ ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። የቱሪዝም ልማቱ በተለይም በገጠር አካባቢዎች ያሉ የሀብት ክፍፍልን ለማስፋፋት እየረዳ ይገኛል። በማህበረሰብ ላይ የተመሰረቱ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች የአካባቢው ማህበረሰቦች እንደ አስጎብኚ፣ ማረፊያ አቅራቢ ሆነው እንዲሰሩ በማስቻል ከቱሪዝም ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review